ብሪክስ ተገዳዳሪ ኃይል ሆኖ የመውጣቱ አንድምታ

10 Days Ago 382
ብሪክስ ተገዳዳሪ ኃይል ሆኖ የመውጣቱ አንድምታ

ብሪክስ ከዓለም አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) 37.3 በመቶ የሚሆነውን የሚይዝ ሲሆን፣ ይህም 14.5 በመቶ ከሆነው የአውሮፓ ህብረት አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ በላይ በሆነ መጠን ይበልጣል።

ብሪክስን የተቀላቀሉት አዳዲስ አባላት ለቡድኑ አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) ከ4 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ቢታመንም፣ እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የዓለም የንግድ ድርጅት እና ብሬተን ውድስ ባሉ ተቋማት ውስጥ ወሳኝ ስፍራ ለማግኘት በሚደረገው ትግል እና በአጠቃላይ ታዳጊ ሀገሮችን ወደ አንድ ለማሰባሰብ በሚደረገው ጥረት ለቡድኑ ከፍተኛ ኃይል እንደሚጨምሩ ይነገራል። ለዚህም ይመስላል የአውሮፓ ህብረት ብሪክስን ለመከታተል እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ከቡድኑ ጋር በትብብር ለመሥራት አቋም ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው።

የአውሮፓ ህብረት በብሪክስ መሥራቿ ቻይና ሀሳብ አመንጪነት እና አስፈጻሚነት እየተካሄደ ባለው ‘ሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሼቲቭ ውስጥ’ ንቁ ተዋናይ መሆኑ የብሪክስን ቀጣይ የተሳካ ጉዞ የሚያመላክት እንደሆነም ይነገራል። በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረት በአይሲቲ በተለይም በሁዋዌ በሚመራው የ5ኛ እና 6ኛ ትውልድ የቴሌኮም ማስፋፊያ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ እና በኤሌክትሪክ መኪኖች ዘርፍ ቻይና ላይ ጥገኛ እየሆነ መምጣቱ ሌላው የብሪክስ ቀጣይ መልካም ዕድል ነው።

እ.አ.አ እስከ 2022 ያለውን የቻይና እና የአውሮፓ ህብረት የንግድ ልውውጥ ስንመለከት ህብረቱ የ627 ቢሊዮን ዩሮ ዕቃ ከቻይና ሲያስገባ፣ ቻይና በአንጻሩ የ230 ቢሊዮን ዶላር ዕቃ አስገብታለች። በአገልግሎት ዘርፍ ያለውን ድርሻ ስንመለከት ደግሞ ቻይና ለህብረቱ የ62 ቢሊዮን ዩሮ አግልግሎት ስታቀርብ፣ ህብረቱ ደግሞ የ46 ቢሊዮን ዩሮ አገልግሎት ለቻይና አቅርቧል። ይህ የንግድ እና አገልግሎት ሚዛን ቻይና በአውሮፓ ህብረት ሀገራት ውስጥ ተፈላጊነቷን እያሳደገች መምጣቷን የሚያሳይ ነው። ለዚህም ነው እንደ ፈረንሳይ እና ጀርመን ያሉ የህብረቱ አባል ሀገራት ከቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት በጥንቃቄ የሚይዙት። ይህ ሁኔታ ለብሪክስም መልካም ዕድል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ከአውሮፓ ህብረት አባላት መካከል ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ብሪክስ እየተገዳደረው ያለው ቡድን 7 አባላት ናቸው።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ያወጣው የ2024 የኢኮኖሚ እድገት ትንበያዎች እንደሚያሳየው የብሪክስ ሀገራት ከቡድን 7 አማካይ 1 በመቶ ዕድገት ጋር ሲነጻጸሩ በአማካይ በ3.6 በመቶ ከፍ ያለ ዕድገት ይኖራቸዋል።

በዚህ የ2024 የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ መሰረት ብሪክስን የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ 6.2 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች። የቡድን 7 ሀገራት ጠቅላላ ሀብት ከብሪክስ ሀገራት በ15 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ ቢሆንም፣ ቀጣይ የሆነ ከፍተኛ ዕድገት እና የአባላትን አቅም እያሳደገ ያለው ብሪክስ በሁለት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ከቡድን 7 ኢኮኖሚ ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን እንደሚችል ትንበያው ያሳያል።

በኢኮኖሚ ዕድገቱ ቻይና እና ሕንድ በ2024 በቅደም ተከተል በ4.6 በመቶ እና በ6.8 በመቶ ቅድሚያውን የሚይዙ ይሆናሉ። ሳዑዲ ዓረቢያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ የነፍስ ወከፍ ሀብቷ ከ105 በመቶ በላይ እንደሚያድግ፤ የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ደግሞ 95 በመቶ ድርሻቸውን እንደሚይዙ ይጠበቃል። ቻይና 85 በመቶ፣ ኢትዮጵያ 75 በመቶ፣ ደቡብ አፍሪካ 60 በመቶ፣ ግብፅ 55 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከ43 በመቶ በላይ ለሚሆነው የዓለም የነዳጅ ምርት የብሪክስ አባላት በሆኑት በሩሲያ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በኢራን እና በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች የተያዘ ነው። የመጀመሪያዎቹ አራት የብሪክስ አባላት ደግሞ 72.5 በመቶ ውድ የምድር ውስጥ ማዕድናት ያላቸው ሲሆን፣ በ2020 በተደረገው ጥናት በዓለም ዙሪያ ከተጣሩ የምድር ማዕድናት መካከል 85 በመቶ የሚሆኑትን የምታመርተው ቻይና ብቻ ናት።

እንደ ኮባልት እና መዳብ ያሉ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ባትሪ፣ የሰርኪዩት ቦርዶችን፣ ሌሎች የኤሌክትሪክ ግብአቶችን እና ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ጨምሮ ሌሎች ለዘመኑ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች የሚመረቱባቸውን ውድ ማዕድናት በብዛት የሚገኙት በእነዚሁ የብሪክስ አባል ሀገራት ውስጥ ነው። ከተጠቀሱት ማዕድናት 59 በመቶ የሚሆኑት የሚገኙት በቻይና፣ ሕንድ፣ ብራዚል እና በግብፅ ነው።

በተለይ በ2050 በቅደም ተከተል በ635 በመቶ እና በ1 ሺህ 170 በመቶ እንደሚያድጉ የሚገመቱት እንደ ግብፅ እና ኢትዮጵያ አዳዲስ የቡድኑ አባላት የብሪክስን ምጣኔ ሀብት ተፎካካሪ ብቻ ሳይሆን ቀዳሚም እንደሚያደርጉት የጂኦ ፖለቲካል ሞኒተር መረጃ ያመላክታል።

ከ"Henley & Partners’" የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በመጪው ጊዜያት በብሪክስ ሀገራት 1.6 ሚሊዮን ሚሊየነሮች፣ 4 ሺህ 716 ሴንቲ ሚሊየነሮች እና 549 ቢሊዮነሮች የሚፈጠሩ ሲሆን፣ ይህም ለብሪክስ ተገዳዳሪነት የማይናቅ ድርሻ ያበረክታል።

በቴክኖሎጂ መስክም የቡድኑ አባል ሀገራት ከፍተኛ ዕድገት እያሳዩ ስለመሆናቸው "የሕንድ ሲሊከን ቫሊ" የሚል ቅጽል ስም የተሰጣት የሕንዷ ቤንጋሉሩ ከተማ ምሳሌ ነች። ቤንጋሉሩ በአሁኑ ጊዜ የ13 ሺህ 200 ሚሊየነሮች መኖሪያ ስትሆን ይህ ቁጥር በ2033 ከ30 ሺህ በላይ እንደሚደርስም ተገልጿል። ይህም ከተማዋን በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ከሚያድጉት ከተሞች አንዷ እንድትሆን አድርጓታል።

ቡድኑ በአባል ሀገራት እና በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ውስጥ ለሚከናወነው የመሠረተ ልማት እና ዘላቂ እድገት ፕሮጀክቶች ሐብቶችን ለማንቀሳቀስ እና አሁን ያሉትን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የፈጠሩትን አድልኦ ለማስተካከል የሚያስችል አካታች የሆነ አዲስ የልማት ባንክ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ብሪክስ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በ3.27 ቢሊዮን የህዝብ ብዛትም የዓለምን 41.13 በመቶ ይሸፍናል። ይህ ቁጥር ብሪክስን ለመቀላቀል የጠየቁ ሀገራት ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ ቡድኑ ከፍተኛውን የህዝብ ቁጥር በመያዝ ተፅዕኖው ከፍ ሊል እንደሚችል ይነገራል። ይህ የህዝብ ብዛት ቁጥር ብቻ ሳይሆን በወሊድ ምጣኔ ቀጣይ ፈተና ይሆናል ተብሎ የተፈራውን የሰው ኃይል ችግር የሚፈታ በመሆኑ ትልቅ ሐብት ነው።

በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የዓለምን ሕዝብ ያቀፈው፣ ስትራቴጂያዊ አካባቢ ላይ ያለው እና በኢኮኖሚውም የዓለምን ከፍተኛ ድርሻ የያዘው ይህ ቡድን የዓለምን ኢኮኖሚ ማዕከል ከምዕራቡ ወደ ደቡቡ የዓለም ክፍል በመቀየር ላይ እንደሚገኝ ተንታኞች ይገልጻሉ።

በለሚ ታደሰ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top