ባለ ደማቅ ገድሏ ሴት አርበኛ - ሸዋረገድ ገድሌ

10 Days Ago
ባለ ደማቅ ገድሏ ሴት አርበኛ - ሸዋረገድ ገድሌ

በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ወረራ ጊዜ ለሀገራቸው አኩሪ ገድል በመፈጸም እና ለኢትዮጵያ ነጻነት ዋጋ በመክፈል ስማቸው ከሚነሱ ሴቶች ግንባር ቀደም ናቸው፡፡

ጣሊያን ኢትዮጵያን ልትወር መሆኑ ሲሰማ በሀገር ተቆርቋሪ ዜጎች በተቋቋመው የሀገር ፍቅር ማኅበር አባልነት በመጀመሪያ ከተመዘገቡት ጥቂት ሴቶች መካከል አንዷ ነበሩ፡፡

ወራሪው ፋሽስት አዲስ አበባ ገብቶ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ የጣሊያንን ባንዲራ ሲተካ ስቅስቅ ብለው አልቅሰዋል፡፡

ለአርበኞች ስንቅ በማቀበላቸው ተከሰው ሹማምንት ፊት ሲቀርቡ፣ "ለአርበኞች ስንቅ ማቀበሌ እውነት ነው፤ ይህንንም ያደረኩት ለሀገሬ ክብር ብዬ ነው፤ ሰው እንኳን ለሀገሩ የእናንተ ወይዛዝርት ሀገራቸው ያልሆነችው ኢትዮጵያን ለመውረር የጣታቸውን ቀለበት ሳይቀር መስጠታቸውን ትናገራላችሁ፤ እኔም ለሀገሬ የሠራሁት ሲያንሰኝ እንጂ አይበዛብኝም" በማለት ነበር ለሀገራቸው ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋገጡት፡፡

በጣሊያን ወረራ ዋዜማ ሐምሌ 1 ቀን 1927 ዓ.ም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ንብረታቸውን ሸጠው አስረክበዋል፡፡

አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ የተወለዱት በደብረ ብርሃን በ1878 እንደሆነ "ሸዋረገድ ገድሌ - የአኩሪ ገድላት ባለቤት /1878-1942/" መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ወላጅ አባታቸው ፊታውራሪ ገድሌ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ያደጉ የንጉሡ ባለሟል እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ሸዋረገድ ገድሌ፤ በሕፃንነታቸው የዘመኑን ትምህርት እየተማሩ፣ ጎን ለጎን የቤት አስተዳደርን ትምህርት እየቀሰሙ እንዲያድጉ ተደረገ፡፡ ዕድሜያቸው ሲደርስም ፊታውራሪ ደቦጭ ለሚባሉ ሰው ተዳሩ፡፡ ባለቤታቸው ድንገት ስለሞቱባቸው ልባቸው በሐዘን በመጎዳቱ ወደ መንፈሳዊው ሕይወት በማዘንበል ገዳም ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ አባታቸው ከገዳም አውጥተው ወደ ቤት መለሷቸው፡፡

የታወቁበትን እና ለሀገር ነጻነት ዋጋ የከፈሉበትን የአርበኝነት ተጋድሎን የጀመሩት በ52 ዓመታቸው ነበር፡፡

በሁለተኛው የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ ሠራዊት በክተት አዋጅ ወደ ሰሜን ግንባር ሲዘምት ከሠራዊቱ ጋር በመሆን ዘምተዋል፡፡  

ጣሊያን የመርዝ ጭስ ተጠቅሞ በፈጸመው ጥቃት የኢትዮጵያ ጦር ሲፈታ አርበኛ ሸዋረገድ እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡

ለጊዜው ድል ያገኘ የመሰለው ጣሊያን በክብር ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ እንደ ተራ ጨርቅ ማዋረድ ጀመረ፡፡ ይህን የእብሪት ድርጊት አይተው እንዳላዩ ማለፍ ያልቻሉት ሸዋረገድ ገድሌ፣ በፋሽስት ወታደሮች ፊት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ወደ አደባባይ ላይ ወጡ፡፡

በወቅቱ የፋሽስት ወታደሮች ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠሩት በአዲስ አበባ ከተማ አደባባይ ቀርቶ በቤት ውስጥ እንኳን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ወይም የአርበኞችን ፎቶግራፍ ደብቆ የተገኘ ሰው ከባድ ቅጣት እንደሚደርስበት ስለሚታወቅ ሸዋረገድ ገድሌ ያሳዩት የአደባባይ ግልጽ ተቃውሞ የፋሽስት ወታደሮችን ያስቆጣ ተግባር ነበር፡፡

እንደተጠበቀውም ሸዋረገድን በቁጥጥር ስር አውለው በጨካኝ ሹማምንቶቻቸው ፊት አቀረቧቸው፡፡ ጀግናዋ ግን ያለምንም ፍርሃት ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ ክብር በሹማምንቶቹ ፊት ተናገሩ፡፡

ይህ ድፍረታቸው በሞት የሚያስቀጣ ቢሆንም በጥቂት መልካም ሰዎች ተማጽኖ የሞት ፍርዱ ወደ እስር እንዲለወጥላቸው ተደርጎ ታስረው ከቆዩ በኋላ ተለቀቁ፡፡ ከእስር ከተለቀቁ በኋላም ጠላትን በምን ዓይነት መንገድ እንደሚያጠቁ ስልት ቀየሱ፡፡

በዚህም በጠላት ውስጥ ሠርገው ከገቡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መረጃ በመሰብሰብ በዱር በገደል ተሰማርቶ ጠላትን ለሚፋለመው የወገን ጦር መረጃ ለማቀበል ወስነው ሥራ ጀመሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ላደፈጡት አርበኞች መረጃውን በሚስጥር ለማድረስ እንደ እንቁላል ነጋዴ ጭድ በተነሰነሰበት ቅርጫት ውስጥ መልእክቱን ደብቀው ማመላለስ ጀመሩ፡፡ ጎን ለጎንም በተቻላቸው መጠን ለአርበኞቹ ስንቅ ያደርሱ ነበር፡፡

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒን ለመግደል ካደረጉት ሙከራ ጋር በተያያዘ አርበኛ ሸዋረገድ ተይዘው ታሰሩ፡፡ የፋሽስት ወታደሮችም ሸዋረገድን በኤሌክትሪክ ገመድ በመግረፍ የግድያ ሙከራው እንዴት እና በማን እንደተፈፀመ እንዲናገሩ ጠየቋቸው፡፡ ሸዋረገድም የሚፈጸምባቸውን ድብደባ መቋቋም አቅቷቸው ራሳቸውን ስተው ወደቁ፡፡ ራሳቸውን ከሳቱበት ሰመመን እስኪነቁ ለአንድ ሳምንት ያህል በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ ተደርጎ ሲነቁ እንደገና ወደተዘጋ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡

ፋሽስቶች የሚፈጽሙት ግፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄዱም ይህንኑ ተግባር በመቃወም በወህኒ ቤት ከአንድ ሳምንት በላይ የረሀብ አድማ አድርገዋል፡፡

እምቢታቸው ያናደዳቸው ፈሽስቶች ከሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር ወደ ጣሊያን በመውሰድ አሲናራ ደሴት በሚገኘው ወህኒ ቤት ውስጥ አሰሯቸው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስከፊ ወህኒ ቤት ውስጥ ህይወታቸው ቢያልፍም አርበኛ ሸዋረገድ ግን ከአንድ ዓመት ከሶስት ወር እስራት በኋላ በህይወት ተርፈው እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡

ወደ አገራቸው እንደተመለሱም ቀደም ሲል የጀመሩትን የመረጃ ሥራ አጠናክረው ከመቀጠላቸውም ባሻገር፣ የአባታቸውን ንብረት በመሸጥ የጦር መሳሪያ እየገዙ በድብቅ አርበኞችን ማስታጠቅ ጀመሩ፡፡

ፋሽስቶች ከሚመኩባቸው ጠንካራ ምሽጎች መካከል በአሁኑ ምዕራብ ሸዋ ጀልዱ ወረዳ ቀድሞ በሜጫና ጅባት አውራጃ የሚገኘው ምሽግ አንዱ እንደነበር ይነገራል፡፡ አርበኛ ሸዋረገድ እና ሌሎች አርበኞች ይህን ምሽግ ለመስበር ወሰኑ፡፡ ሚያዝያ 8 ቀን 1932 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን በምሽጉ የነበሩት የፋሽስት ወታደሮች ተሰባስበው እራት በመብላት ላይ ነበሩ፡፡ በጀግኒት ሸዋረገድ ገድሌ አስተባባሪነት በደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን መሪነት 14 የሚሆኑ ጀግኖች በምሽጉ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲያደርሱ ጠላት እራሱን ለመከላከል ባለመቻሉ በምሽጉ ውስጥ የነበሩትን የፋሽስት ወታደሮችን በሙሉ ገድለው 400 ባንዳዎችን ማረኩ፡፡ በርካታ የጦር መሣሪያዎችንም ከማረኩ በኋላ ምሽጉን ሙሉ በሙሉ በእሳት አጋዩት፡፡

በዚህ የተበሳጨው ጣሊያን አርበኞችን አድኖ ለመያዝ በርካታ ጦር ቢልክም ቀድመው ቦታ ይዘው የነበሩት የኢትዮጵያ ጀግኖች ጠላትን በተኩስ አጣድፈው በታተኑት፡፡

በሌላ ጊዜ ደጃዝማች ዘውዴ ጥላሁን ከሸዋረገድ ጋር በተመካከሩት መሰረት የአዲስ ዓለም (ኤጄሬ) ምሽግ ለመስበር እቅድ አውጥተው የአካባቢውን ሰዎች አማክረው ፈቃደኝነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሸዋረገድ ገድሌ ዘንድ ሰዎችን ልከው ለደህንነታቸው አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ አሳሰቡአቸው፡፡

አርበኛ ሸዋረገድ አካባቢውን ከመልቀቃቸው በፊት ልጅ ጃገማ ኬሎ (በኋላ ሌተናል ጄኔራል) በእቅዱ እንዲሳተፉ ተነጋግረው አዘጋጁአቸው፡፡ አርበኞቹ ተገናኝተው የአካባቢውን መውጫ መግቢያ ካጠኑ በኋላ ደጃዝማች ዘውዴ፣ ልጅ ጃገማ ኬሎ እና መቶ አለቃ ወልደ ዮሐንስ ተክሉ ባዘጋጁት የማጥቃት ስልት መሰረት ምሽጉን የማፍረስ እርምጃው እንዲከናወን ተወሰነ፡፡

በእቅዳቸው መሠረት በምሽጉ ዘበኞችና በተጠመደው የጠላት መትረየስ ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር እና የእሩምታ ተኩስ በመክፈት የማጥቃት እርምጃውን ጀመሩ፡፡ በዚህም የወገን ጦር ላይ እምብዛም ጉዳት ሳይደርስ በታቀደው መሠረት የተሳካ ሥራ ተሠራ፡፡

በዚህም ፋሽስት በግፍ በወህኒ ቤት አስሮ ሞታቸውን ይጠባበቁ የነበሩትን እስረኞች ያለአንዳች ጉዳት ከእስር ቤቱ ሰብረው እንዲወጡ ተደርጎ የጠላት የመሳሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤቱም ተዘረፈ፡፡

ከአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ በኋላ መቂ አካባቢ ከሻለቃ በቀለ ወያ ጦር ጋር ተሰልፈው ወደ ግንባር ውጊያ ተቀላቅለዋል፡፡ በኋላም ጅማ አካባቢ ከነበረው የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋር ለመገናኘት ተጓዙ፡፡ በዚያም ጠላት ድንገተኛ አደጋ ጥሎ ለአራት ሰዓት ያህል ተዋግተው ተማረኩ፡፡ እንደገና ወደ እሥር ቤት ተወስደውም የፊጥኝ ታሠሩ፡፡ በ1933 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ ነጻ ስትወጣ ሸዋረገድ ገድሌ አርበኞችን ወደ መርዳት እና የበጎ አድራጎት ሥራን ወደ መሥራት ገቡ፡፡

በኋላም ወደ መንፈሳዊ ህይወት በማዘንበል ወደ ግሽን ማርያም እና ሌሎች ገዳማት በመጓዝ በፆም ፀሎት ተወስነው ቆይተዋል፡፡

ቅዱስ ላሊበላን ተሳልመው እዚያው እያሉ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ጥቅምት 22 ቀን 1942 ዓ.ም በተወለዱ በ 64 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ለሥራቸው መታሰቢያ የሚሆን በአዲስ አበባ ወደ ቀበና የሚወስደው መንገድ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡ ሲሞቱም እንዲህ ተብሎ እንተገጠመላቸው የህይወት ታሪካቸው ያሳያል፡-

እናንት ወጥ ቤቶች በርበሬ ቀንጥሱ፣

እናንት ሥጋ ቤቶች ሰንጋውን ምረጡ፣

ሸዋረገድ ገድሌ ለገና ሲመጡ፤

ቤተሰቧ ሰፊ ገናና ጥምቀት፣

ሸዋረገድ ገድሌ እንደምን ትሙት፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top