በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት የብድር መጠን 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡- ብሔራዊ ባንክ

10 Days Ago 164
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት የብድር መጠን 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡- ብሔራዊ ባንክ
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት የብድር መጠን 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ።
 
አይካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው 7ኛው የምስራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናንስ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን አብራርተዋል።
 
ከምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም በአህጉሩ ትስስርን ለመፍጠር፣ በዲጂታል ፋይናንስ፣ የተረጋጋ የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍጠር፣ አካታችነት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንም ዘርዝረዋል።
 
በተደራሽነት፣ በአገልግሎት ስብጥር፣ በዲጂታል ፋይናንስ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ በዘመናዊ ስጋት አስተዳደርና ሌሎችም አሰራሮች እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
 
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉ በተደራሽነት፣ በተቀማጭ ገንዘብ፣ በአጠቃላይ የሀብት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ስለመምጣቱም ተናግረዋል።
በ2024 መጀመሪያ የፋይናንስ ተቋማት 121 መድረሳቸውን ጠቅሰው፤አጠቃላይ ሐብታቸው ደግሞ 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን እንዲሁም ተቀማጭ ገንዘባቸው 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል።
 
በተመሳሳይ የብድር መጠናቸውም 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም ነው የተናገሩት።
 
የኢትዮጵያ መንግስት የተረጋጋ የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍጠር ትኩረት መስጠቱን ያነሱት ገዥው፤ በዚህም ጤናማ የፋይናንስ ዘርፍ ማስቀጠል ችሏል ብለዋል።
 
መንግስት ተግባራዊ እያደረጋቸው ባሉ ስትራቴጂዎች ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ፣ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የአገልግሎት ስብጥርን ማስፋት፣በዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች መሰረት መስራትና በፈጠራና ቴክኖሎጂ የታገዘ የፋይናንስ ዘርፍ እውን ለማድረግ ያስችላሉ ነው ያሉት።
 
ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ ፈጠራና ውድድርን በማፍጠን መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
 
በዘርፉ የተደረገው የፖሊሲ ለውጥ የውጭ ኢንቨስተሮች ገብተው እንዲሰሩ በማድረግ አዲስ ካፒታል ለማምጣትና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮን ለመውሰድ እንደሚያስችልም አንስተዋል።
 
ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ከማድረግ ጎን ለጎን የካፒታል ገበያን በማቋቋም ላይ መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ገበያው በዚህ ዓመት መጨረሻ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ኢንቨስትመንት ባንክ፣ አማካሪ ድርጅቶችን ማካተት በፋይናንስ ዘርፉ አዲስ ምህዳር እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
 
በተጨማሪም ቁጠባን ለማሳደግ አማራጮችን ለማስፋት ምቹ ሁኔታዎችን ለድርጅቶች ይዞ መጥቷል ነው ያሉት።
 
የምስራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናንስ ጉባኤ በምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ ትስስርን ለማጠናከር፣ ልምድና ተምክሮ ለመለዋወጥና አለም አቀፍና ቀጣናዊ ስጋቶችን በጋራ መፍትሔ ማበጀት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚደረግበት ነው።
 
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው 7ኛው የፋይናንስ ጉባኤ የባንኮች ሃላፊዎች፣ የኢንሹራንስ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተዋንያን እየተሳተፉ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top