ባለፉት 6 ዓመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

5 Mons Ago 645
ባለፉት 6 ዓመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ባለፉት ስድስት ዓመታት በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መስኮች የተለያዩ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል።

ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱንም ነው በመግለጫቸው ያነሱት።

በባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ስኬቶች መመዝገባቸውን ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ የኢትዮጵያ ብሪክስ አባል መሆን ትልቅ ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎች እንዲመለሱ ከማድረግ ባሻገር የዜጎች መብትና ክብር እንዲጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ባለፉት ቀናት በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከአራት ሺ ሁለት መቶ በላይ ዜጎች በአስራ ሁለት በረራዎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ሳምንታት ይህ ዜጎችን የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሳምንቱ የተለያዩ የውጪ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ፤ ኢትዮጵያ እና ጃፓን በቶኪዮ የፖለቲካ ምክክር ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።

በዚህ ምክክር ላይም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ በሚያጠናክሩ ሁኔታዎች ላይ ውይይት መደረጉን እና በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

በሲዊዘርላዊ የሰብአዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መካሄዱን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፤   በዚህ ዝግጅትም በተፈጥሮና ሰራሽ ምክንያት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚውል የ 630 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ቃል መገባቱን አንስተዋል።  

የኢትዮ ሳውዲ የጋራ ሚኒስትሮች ጉባኤ በመጪው ግንቦት በኢትዮጵያ እንደሚደረግ ያስታወቁ ሲሆን ለዚህም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በወንደወሰን አፈወርቅ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top