የኢትዮጵያ ህልም የነበረው ኅብረት ተሳክቷልን?

10 Mons Ago 1570
የኢትዮጵያ ህልም የነበረው ኅብረት ተሳክቷልን?

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እና በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩት ሀገራት ነጻነት የከፈለችው ዋጋ ውድ ነው፡፡ ነጻነቷን ጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ ብቻዋን የመንግሥታቱ ማኅበር አባል በነበረችበት ወቅት የአውሮፓውያንን የግፍ ወረራ አውግዛለች፤ ብቻዋንም በፍትህ አደባባይ ቆማለች፡፡ የኢትዮጵያ የፍትህ አደባባይ ጩኸት የገለጠው የአውሮፓውያን ግፍ አውዳሚው የሁለተኛ ዓለም ጦርነት እንዲከሰት አድርጓል፡፡ ይሁንና ከታሪክ ያልተማረው ዓለም አሁንም ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካን እና የጭቁን ሕዝቦችን ጩኸት እየሰማ ባለመሆኑ ዓለም መከራ ውስጥ እንድትኖር አድርጓታል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ኅብረቶችን መሥራች ሆና በአባልነት የምትቀላቀለው በዓለም ላይ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ጉልበተኞች አቅመ ቢሶችን እንዳይጨፈልቁ እና ሁሉም የዓለም ሕዝብ በእኩልነት የመኖር መብቱ እንዲከበርለት ነው፡፡

ለዚህም ነው ራሷ ነጻነቷን ስላስከበረች በቃ ብላ ያልተቀመጠችው፡፡ አፍሪካውያን ወንድሞቿ ነጻ ሳይወጡ ነጻነቷ ሙሉ ስለማይሆን አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲሆኑ የታገለችው፡፡ የዓለምን ፍትህ የማይሻው የምዕራባውያኑ ጎራ ይህን የኢትዮጵያን ጥረት ለማሰናከል እና አፍሪካን ድምጽ አልባ ለማድረግ ዛሬም ኢ-ፍትሃዊ ጫናውን እንደቀጠለ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አፍሪካ ነጻነቷን እንድታገኝ ካደረገቻቸው ትግሎች ጎን ለጎን አፍሪካውያን ኅብረት ፈጥረው የሚደርስባቸውን ጫና እንዲቋቋሙ እና ሕዝቦቻቸው ወደ ተሻለ ህይወት እንዲሸጋገሩ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ጋና በ1949 ዓ.ም ነጻነቷን በማግኘት የጀመረችው ጉዞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከተመሠረተበት ግንቦት 1955 ዓ.ም ድረስ 32 ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ሆኑ፡፡ እነዚህ ሰላሳ ሁለት ሀገራትም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረቱ፡፡

ኢትዮጵያ እና ሌሎች የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች ድርጅቱን ለመመሥረት ያነሳሳቸው ነጻነታቸውን ያላገኙ ሀገራት ነጻ እንዲሆኑ ነጻነታቸውን ያገኙት ደግሞ ነጻነታቸው ሙሉ እንዲሆን ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ኅብረት ላይ ያላት አቋም በመሪዎቿ መቀያየር የማይናወጽ በየዘመናቱ ኅብረቱ ጠንካራ ሆኖ እንዲዘልቅ የየዘመኑን ጥያቄ ለመፍታት መሪዎቿ ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ድረስ ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች ያለልዩነት የድርሻቸውን ተወጥተዋል እየተወጡም ነው፡፡

 

የኢትዮጵያን መሻት ያሳየው የካዛብላንካ እና የሞኖሮቪያ ውህደት

ድርጅቱ ገና የምሥረታ ሀሳቡ ሲጠነሰስ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች ያላቸው ቡድኖች ተፈጠሩ፡፡ እነሱም የሞኖሮቪያ እና የካዛብላንካ ቡድኖች ናቸው፡፡ እራሱን “የዘመናዊ እና ተራማጅ አስተሳሰብ አቀንቃኝ” ብሎ የሚጠራው እና በጋናው ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራው የ“ካዛብላንካ ቡድን” ሲሆን፣ ቡድኑ አፍሪካ በኅብረት መዋሀድ አለባት የሚል ዓላማ የያዘ ነበር፡፡ አባላቱም ጋና፣ አልጄሪያ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ማሊ እና ሊቢያ ነበሩ።

ሁለተኛው የ”ሞንሮቪያ ቡድን” ሲሆን የተመራው በሴኔጋሉ ፕሬዚደንት ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንግሆር ነበር። አባላቱ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ እና ኢትዮጵያ ሲሆኑ የነሱ ሀሳብ ደግሞ በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ኅብረት መመሥረት አዳጋች ስለሆነ የአንድነት ድርጅት ተመስርቶ በሂደት ወደ ኅብረት ማደግ አለበት የሚል ነበረ።

በዚህ መሀል ገለልተኛ ሆነው ወደ የትኛውም ቡድን ያልተቀላቀሉ ሀገራትም ነበሩ፡፡ እነዚም ቤኒን፣ ቱኒዚያ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ቶጎ፣ ሶማሊያ፣ ኮትዲቯር፣ ኬንያ፣ ኮንጎ፣ ጋቦን፣ ማዳጋስካር፣ ሞሪታኒያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቡርክና ፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን፣ ኒጀር፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ማላዊ ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያም በወቅቱ የነበረውን የዓለም ሁኔታ፣ ሀገራቱ የነበሩበትን የሥነ-ልቦና ደረጃ እና ውጫዊ ተጽዕኖዎችን ከግምት በማስገባት ሁለቱን ቡድኖች በማግባባት እና ሁሉንም ያካተተ ድርጅት የመመሥረት ትልቅ የቤት ሥራ ወስዳ ሥራ ጀመረች፡፡ የኢትዮጵያ እና የአጋሮቿ የወቅቱ አቋም የነበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመስርቶ የማሰባሰቡን ሥራ ከሰራ በኋላ ወደ ኅብረት እና ውህደት እንዲሄድ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቶቹ በወቅቱ ሁሉም ሀገራት ሙሉ በሙሉ ከቅኝ አገዛዝ ስላልተላቀቁና በዚህ ሁኔታ የሚፈጠረው ኅብረትም የተሟላ ስለማይሆን፣ በሌላ በኩል ነጻነታቸውን ያገኙ ሀገራትም ቢሆኑ ከቅኝ ገዢዎቹ የሥነ-ልቦና ጫና ባለመላቀቃቸው ይህም እንኳን ወደ ውህደት የሚሄድ ኅብረት ቀርቶ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እንኳን ለመግባባት ከባድ ስለሚሆን ነበር፡፡

በዚህም መሰረት በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረት እና በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በሳል ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ እንዲገናኙ ተደርጎ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ሀሳብ ተስማሙ፡፡ በስምምነቱ መሠረትም ገለልተኛ የሆኑ ሀገራትንም ጨምሮ 32ቱ ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ቻርተር እንዲፈርሙ ተደርጎ ድርጅቱ ተመሰረተ።

በቻርተሩ ላይ እንደተገለጸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ዓላማ የአፍሪካ ሀገራትን አንድነት እና ኅብረት ማጎልበት፣ ለአፍሪካ ሕዝብ የተሻለ ህይወት ለማምጣት የሚያደረጉትን ትብብሮች እና ጥረታቸውን በማጠናከር ውጤታማ ማድረግ፤ የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት እና የግዛት እንድነት መጠበቅ፣ የቅኝ ግዛት እና አፓርታይድን ከአህጉሪቱ ማስወገድ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀፍ ውስጥ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲኖር ማድረግ እና የአባል ሀገራቱን የፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የትምህርት፣ የባህል፣ የጤና፣ የደህንነት እና መከላከያ ፖሊሲዎችን ማቀላጠፍ ናቸው።

ለመሆኑ ኅብረቱ ዓለማውን አሳክቷል?

ያኔ የነበሩት አርቆ አሳቢ አባቶች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሲመሰርቱ ድርጅቱ የአህጉሪቱን አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ከሠራ በኋላ ወደ ኅብረት እና ውህደት እንደሚያድግ ተስፋ እንደነበራቸው ቻርተሩ ላይ የሰፈረው ሀሳብ ይጠቁማል፡፡ ታዲያ ዘንድሮ 65ኛ ዓመቱን የሚያከብረው የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ1994 ዓ.ም ደርባን ላይ ተሰብስቦ የአፍሪካ ኅብረት መሆኑን ከማወጁ ባሻገር አህጉሪቱን ወደ ፊት ሊያሻግሩ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ችሏልን?

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት የአህጉሪቱን ሁኔታ ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ THIRD WORLD RESURGENCE የተባለ ድረ-ገጽ ላይ እንደተጻፈው ኅብረቱ ከዓላማዎቹ ያሳካው አህጉሩን ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ግዛት ነጻ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ 

አፍሪካ አሁንም ከቅኝ ግዛት ዘመን ባልተናነሰ የግጭት፣ የርሃብ፣ የስደት እና የሰቆቃ ምድር መሆኗ ለዚህ ዋና መገለጫ መሆኑን በድረ-ገጹ ሰፍሯል፡፡ እንደ ፓን አፍሪካን የዜና ወኪል፣ ፓን አፍሪካን የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት፣ የፓን አፍሪካ ፖስታ ኅብረት እና የአፍሪካ ብሔራዊ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ድርጅቶች ኅብረት ያሉ ድርጅቶችን ለማሳካት አሁንም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩም ኅብረቱ ዓለማውን እያሳካ ላለመሆኑ እንደ ማሳያ ይቀርባል።

የኅብረቱ አባል ሀገራት ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት ሲነግስ፣ በየጊዜው መፈንቅለ መንግሥታት ሲደረጉ፣ የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ዛሬም አፍሪካን የመከራ ምድር ሲያደርጓት ሲፈልጉም እንደሊቢያ ባሉት ሀገራት ላይ ዘመቻ ከፍተው መንግሥት ሲያፈርሱ ኅብረቱ መግለጫ ከማውጣት በስተቀር ምንም ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉም ሌላው ማሳያ ነው፡፡

በእርግጥ እዚህ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች የነበሩት 32 የአህጉሪቱ መሪዎች በተለይ ከቅኝ ግዛት መላቀቅ በኋላ ፊታቸውን ወደ ልማት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ አለማዞራቸው አንዱ ችግር መሆኑ ይነሳል። ይልቁንም ህብረቱ እንዲመሰረት ትልቅ ጥረት ያደረጉት መሪዎች የስልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም ባደረጉት ጥረት አሊያም የሀገራቸውን ችግሮች ለመፍታት ባሳዩት ዳተኝነት ብዙ ነጻ አውጪዎች እንዲፈጠሩ እና እንዲፋለሟቸው አድርጓል። እዚህ ላይ ታዲያ እነዚህ ህብረቱ እንዲፈጠር ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የሰሩት መሪዎች ከልጣን የተወገዱት በአብዛኛው በመፈንቅለ መንግሥት መሆኑ የአህጉሩን ችግር ይበልጥ አዋሳስቦታል። የነጻነት ብርሃን እንደታየ ብዙ ተስፋ እንደተሰነቀ የተጀመረው መፈንቅለ መንግሥት አሁንም የአህጉሪቱ መለያ እና ያልተሻገረችው ችግር ሆኗል።

ኬኒያዊው የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ፕሮፌሰር ፓተሪክ ሉሙምባ እንደሚሉት አፍሪካ የጋራ የመገበያያ ገንዘብ ሳይኖራት፣ ያለቪዛ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ መዘዋወር ካልተቻለ እና አፍሪካ የራሷን ዕድል በራሷ መወሰን አቅቷት የሌሎችን ምጽዋት ጠባቂ እስከሆነች ድረስ ነጻነቷን ተጎናጽፋለች ማለት አይቻልም፡፡አሁንም አፍሪካ በ”ኒዎ ኮሎኒያሊዝም” ውስጥ ስለሆነች ከምዕራባውያን ቅኝ ግዛት አልተላቀቀችም ይላሉ፡፡

ራሷን ችላ ለሌሎች የሚተርፍ በቂ የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ኃይል ያላት አፍሪካ ኅበረቷን አጠናክራ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዳትሆን ያደረጓት ደግሞ መሪዎቿ ራሳቸው መሆናቸውን ፕሮፍሰሩ ይናገራሉ፡፡ ሁሌም ሌብነት እና የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ያሉት የአህጉሪቷ መሪዎች የአፍሪካ ሀብት እንዲበዘበዝ እና ወጣቷ የስደት ሰለባ እንዲሆን አድርጓልም ይላሉ፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ራዕይ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት እና ውህደት መቼ እውን ይሁን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ኢትዮጵያ አሁንም የራሷን ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገች ቢሆንም፣ የሌሎች አባል ሀገራት ይሁንታ እና ቁርጠኝነት ካልታከለበት ሊሳካ እንደማይችል የእስከአሁኑ ጉዞ ማሳያ ነው፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top