ሩዋንዳ ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል አዲስ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) አስተዋወቀች

1 Yr Ago 595
ሩዋንዳ ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል አዲስ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) አስተዋወቀች

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የሀገሪቱ የምርመራ ቢሮ እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም የአካባቢ ሥነ-ምህዳር ላይ ይፈጸማሉ የተባሉ ህገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ወስነዋል።

ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ መረጃ በመሰብሰብ፣ የመከላከያ ፍተሻ በማካሄድ በአካባቢ ሥነ-ምህዳር ላይ የሚሰሩ ወንጀሎችን ምርመራ እንደሚደግፉ ጋዜጦቹ ዘግበዋል።

የሩዋንዳ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ዣን ዲ አርክ ሙጃዋማሪያ እንደተናገሩት "ሰው አልባ አውሮፕላኖቹ እንደ መሬት መራቆት፣ የውሃ ብክለት እና ሌሎች የአካባቢ ሥነ-ምህዳር ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ይረዳሉ"።

መንግሥት ሊቆጣጠር ከሚፈልጋቸው ተግባራት መካከል ህገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት፣ የውሃ ብክለት፣ ህገ-ወጥ የእንጨት ስንጠቃ እንዲሁም ጥበቃ የሚደረግላቸው እንደ ፓርኮች እና የወንዝ ዳርቻዎች ወረራ እንደሚገኙበት ሲቲዝን ዲጂታል ዘግቧል።

የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሯ "የሩዋንዳ ምርመራ ቢሮ የአካባቢ ሥነ-ምህዳር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በምንሰራው ሥራ ላይ  ከኛ ጎን በመሆኑ እናመሰግናለን" ብለዋል።

ሀገሪቱ የረዥም ጊዜ የአረንጓዴ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ስትራቴጂ እና እ.አ.አ በ2030 የበካይ ጋዝ ልቀትን በ38 በመቶ ለመቀነስ የታለመ የአየር ንብረት የድርጊት መርሃ ግብር እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top