የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸው ብዘሃ ኢንቨስትመንት ከመፍጠር ባለፈም ሰፊ የስራ ዕድልና ትስስርን እየፈጠሩ እንደሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮፖሬሽን አስታወቀ፡፡
በኢኮኖሚ ዘርፉ ላይ በተደረገው ሪፎርም በአሰራር ደንብና መመሪያዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ በመደረጉ የኢንቨስትመን ዘርፍ መነቆዎችን በመፍታት ለዓለም አቀፍ አልሚዎች ምቹ የኢንቨሰትመንት አማራጭ እንዲፈጠር ማድረጉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጁነዲ ገልፀዋል፡፡
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ካሏቸው 177 ሼዶቸ 150 በሀገር ውስጥ እና በውጭ ባለሀብቶች መያዛቸውን የገለፁት አቶ ዘንን በጅማ፤ ባህርዳርና ሐዋሳ ያሉ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን እየሳቡ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡
በድሬድዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የተጀመረው የሎጅስቲክና ንግድ አዲስ እሳቤ ብዝሃ ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተናገረዋል፡፡
የቦሌ፣ ለሚና አዳማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ባለሀብቶች መያዛቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ80 በላይ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች መግባታቸውን የገለፁት ምክትል ሃላፊው፤ 17 የተለያየ መጠንና አይነት ያላቸው ሼዶችን ወስደው ማሽን በመትከል ወደ ስራ በመግባት ላይ እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡
በሁሉም የኢኮኖሚ ዞኖች ከ85 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውም ጠቁመዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና መካከል አስሩ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸው ይታወቃል፡፡
በሐይማኖት ከበደ