በዘመናት ዥረት ውስጥ የማይለወጠው የእናት ፍቅር

20 Hrs Ago 118
በዘመናት ዥረት ውስጥ የማይለወጠው የእናት ፍቅር

በየጊዜው በሚለዋወጠው ዓለም ውስጥ በምንም ነገር ሳይበገር የሚቀጥል አንድ ኃይል አለ - ­የእናት ፍቅር። 

የእናት ፍቅር ከትውልድ ወደ ትውልድ የማይደበዝዝ፣ ቅድመ ሁኔታ የሌለው እና ዘላለማዊ መሆኑን በዘመናት ሽግግር ውስጥ አረጋግጧል።

በቀደመው ዘመን ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት መነሣትን፣ እሳት ሥር ተደፍቶ የጣፈጠ ምግብ ማዘጋጀትን፣ ውኃ ለመቅዳት ረዥም ኪሎ ሜትሮች በእግር መጓዝን ጨምሮ ብዙ ተዘርዝረው የማያልቁ የእናትነት ፍቅር መግለጫዎች ነበሩ።

የዛሬዎቹ እናቶችም ልጆቻቸውን በተመሳሳይ ቁርጠኝነት እያሳደጉ ሥራን፣ ትምህርትን እና ዲጂታል ሕይወትን በማመጣጠን ላይ ናቸው።

ከረዥም የሥራ ቀን በኋላ የቤት ውስጥ ሥራን በመሥራት፣ ልጅን በመንከባከብ፣ በማስጠናት ለነገ ውሏቸው በመዘጋጀት ይጠመዳሉ።

በገጠር መንደሮችም ሆኑ በተጨናነቁ ከተሞች ውስጥ ያሉ እናቶች፣ ከፀሐይ በታች ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ለልጆቻቸው የሚናገሩት አንድ ዓለም አቀፋዊ እውነት አለ - “እዚህ ያለሁት ላንተ/ላንቺ ነው" የሚል።

የእናት ፍቅርን ልዩ የሚያደርገው ቅድመ ሁኔታ የሌለው፣ በታላቅ ዝምታ ውስጥ የሚገለጽ፣ ጥንካሬው ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑ ነው።

እናቶች ለልጆቻቸው ፍቅራቸውን የሚገልጹት በሚያረጋጋ መንፈስ በስስት በማየት እና ከልብ በማቀፍ ነው።

እናት ፍቅር በጊዜ መፈራረቅ ውስጥ የመግለጫ መንገዱ ቢለያይም በምላሹ ምንም የማይጠይቅ፣ ሁሉንም ነገር የሚሰጥ የፍቅር ዓይነት ነው።

እናቶች ዓለም በዝግመተ ለውጥ ላይ ባሳለፈችባቸው ጊዜያት ሁሉ የሰዎች መጽናኛ፣ ጠንካራው ጋሻ እና የማይጠፉ ብርሃን ናቸው።

በትውልዶች መካከል በዘመን ዥረት ውስጥ ላለፉ ለሁሉም እናቶች ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል።

መልካም የእናቶች ቀን!

በሴራን ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top