በዝናብ ወቅት አሽከርካሪዎችና እግረኞች በቴክኒክ ጉድለት ከሚደርሱ አደጋዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ አስታወቀ፡፡
ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለአደጋ አጋላጭ ሁኔታዎችን ለመቀነስ እንዲያስችል አሽካሪካሪዎችና እግረኞች ማወቅ አለባቸው ያሉትን ቅድመ ጥንቃቄ በተመለከተ በአዲስ አበባ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የህዝብ ግንዛቤ ኃላፊ ኢንስፔክተር ዳዊት ሙሉጌታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የግልም ሆነ የብዙኃን ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የጎማ ጥርስ ያለቀባቸውን ወይም የላሸቀና የለሰለሰ ጎማ ያላቸውን ተሽከርካሪዎች በዝናብ ወቅት ለአደጋ ስለሚያጋልጡ ጎማ መቀየር አሊያም ማቆም ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
አሽከርካሪው በዝናብ ወቅት የተሽከርካሪውን መስታወት መጥረጊያ ዋይፐር እንደሚሰራና እንደማይሰራ በየእለቱ ማረጋገጥ አለበት ያሉት ኢንስፔክተር ዳዊት፤ ይህም የሾፌሩን እይታ በመገደብ ላልተጠበቀ አደጋ ስለሚያጋልጠው ቀድሞ መጠንቀቅ አለበት ብለዋል፡፡
እነዚህንና መሰል ችግሮች በተለይም የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚታዩ የቴክኒክ ጉደለቶች በመሆናቸው አደጋ ከማድረሳቸው በፊት የግዴታ መቀየር ያለባቸው ናቸው ተብሏል፡፡
የብዙኃን ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች በዝናብ ወቅት መስታወት ግጥም አድርገው ከመዝጋት መቆጠብ አለባቸው የሚሉት ኢንስፔክተር ዳዊት፤ መስኮቱ ሲዘጋ የሰዎች ትንፋሽ የመኪናውን መስታወት ይሸፍነዋል፣ አየር ወደ ተሽከርካሪው ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን ይፈጠራሉ ብለዋል፡፡
አሽከርካሪዎች በዝናብ ወቅት የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ በእምነት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሲደርሱ በዝግታ በመንዳት የሚደርሱ አደጋዎች መቀነስ አንደሚችሉም ገልፀዋል፡፡
በዝናብ ወቅት የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ከአንድ ተሽከርካሪ ወደ ሌላኛው ሲሸጋገሩ የወረዱበት መኪና ማለፉንና አለመደረቡን ማረጋገጥና በእግረኛ መንገድ መኪና አለመኖሩን አይተው መሻገር አለባቸው ብለዋል፡፡
እግረኞችና የብዙኃን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ከዝናብ ለመከላከል የሚጠቀሙባቸውን ዣንጥላዎች እይታን በማይገድብ መልኩ ከፍ አድርገው በመያዝ ራሳቸውን ከአደጋ መጠበቅ እንዳለባቸውም ኢንስፔክተር ዳዊት የግንዛቤ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በከተማው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ እግረኞች ጭንቅላትን በመሸፈን፣ የጆሮ ማዳመጫ አድርጎ ሙዚቃ እየሰሙ መሄድ በዝናብ ወቅት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ በማወቅ መጠንቀቅ አለባቸው ብለዋል ኢንስፔክተር ዳዊት፡፡
አሽከርካሪዎች በከተማ ውሥጥ የተተከሉ 30፣ 40፣ 50 የፍጥነት ገደብ ምልክቶችን በመጠቀም ለአደጋ መንስኤ የሚሆኑ ሁኔታዎችን መቀነስ አለባቸው ሲሉም ኢንስፔክተሩ ለኢቢሲ ዶትስትሪም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ