በመላው የዓለም ሀገራት ቋንቋዎች እና ባህሎች፣ ወግ እና ሥርዓቶች ይለያዩ እንጂ የእናት ፍቅር መገለጫው ተመሳሳይ ነው።
ታዲያ ለዚህች ፍቅሯ ለማይቀየር እናት ከተለያዩ የምድር ማዕዘናት፣ ወንድ እና ሴት፣ ትልቅ፣ ትንሽ ሳይል ሰዎች እውነተኛ እና በፍቅር የተሞሉ ደብዳቤዎችን ጽፈዋል።
በዚህ የእናቶች ቀን ለእናቶች የተላኩ ደብዳቤዎች ውስጥ የተገለጹ ማራኪ ሐረጎችን እንመልከት፦
“እኔን ማህፀንሽ ውስጥ ብቻ አልነበረም የተሸከምሽኝ፤ በልብሽ እና በሐሳብሽም ተሸክመሽኛል። አሁንም ደግሞ በጸሎትሽ ተሸከምሽኝ”። - ማሪያ፣ ፊሊፒንስ
"ሁሌ በር ላይ ቆመሽ ትጠብቂኝ ነበር። ወደ ቤት ዘግይቼ ስመጣም እዛው ነሽ - በንዴት ሳይሆን በፍፁም ፈገግታ።” - ግሬስ፣ አየርላንድ
"አንድም ቃል ሳልናገርም የምፈልገውን ሁልጊዜ ታውቂያለሽ፤ ይህ ግን አስማት አይደለም፤ የእናት አዕምሮ ነው” - አሕመድ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ
“ይቅርታ ከመጠየቄ በፊት ይቅር ብለሽኛል። ይህን የሚያደርገው ማነው? እናት ብቻ" - ራያን፣ ካናዳ
“ሳቅሽ የልጅነቴ ማጀቢያ ነበር፤ ያንን ሳቅ በየቀኑ እናፍቀዋለሁ። - ኖህ፣ አውስትራሊያ
"እንዴት እንደደከመሽ አላስታወቀብሽም፤ ምክንያቱም እንዲታይ ፈጽሞ አትፈቅጂምና"። - ባኦ፣ ቬትናም
"ቤት ውስጥ የነበረውን ብቸኛ ምግብ ለኔ ሰጠሺኝና አንቺ እንዳልራበሽ ነገርሽኝ፤ ነገር ግን ያኔ ሆድሽ ባዶ መሆኑን ለመረዳት በጣም ትንሽ ነበርኩ። - ሳሙኤል፣ ኬንያ
"ልጅ እያለሁ እንዴት እንደምሄድ አስተምረሽኛል፤ አሁን ደግሞ ሕይወት ስትሰብረኝ እንዴት እንደገና እንደምቆም አስተማርሽኝ።” - ካርሎስ፣ ሜክሲኮ
“እማ፣ እጆችሽ ናፍቀውኛል። እነሱ የመጀመሪያ ቤቴ ነበሩ፤ በጣም አስተማማኝ ቦታዬ ናቸው፤ በዓለም ላይ ያለ የትኛውም እቅፍ እንዳንቺ ተሰምቶኝ አያውቅም"። - ፕሪያ፣ ሕንድ
“እናቴ፣ አንድ ጊዜ እንኳ ስታርፊ አይቼሽ አላውቅም፤ አሁን ሲገባኝ ያኔ ‘ደኅና ነኝ’ የምትይው ለኔ ስትይ መጠንከር ስለነበረብሽ እንደሆነ ገብቶኛል"። - ሊና፣ ጀርመን
"ሕልምሽን ለኔ ሰጥተሽ ጭንቀትሽን ሁሉ በዝምታ ተሸክመሻል፤ አሁን ላኮራሽ ብቻ ነው የምፈልገው"። - ፉአድ፣ ሳውዲ አረቢያ
“እናቴ መሆንሽን በጣም የምትወጂው ነገር እንደሆነ በአንድ ወቅት ነግረሽኝ ነበር፤ እኔም ልንገርሽ፣ ያንቺ ልጅ መሆን ትልቁ ስጦታዬ ነው።” - ላይላ፣ ሞሮኮ
“ምንም ጠይቀሽኝ አታውቂም፣ ግን ሁሉንም ነገር ሰጠሽኝ፦ ጊዜሽን፣ ወጣትነትሽን፣ ሕልምሽን”። - ናዲያ፣ ግብጽ
"እኔ ስወድቅ አንስተሽ አላቀፍሽኝም፤ በራሴ መቆም እስክችል ድረስ ከጎኔ ተንበረከክሽ እንጂ”። - ኢዛቤል፣ ፈረንሳይ
“ፍቅር ጫጫታ እና ጋጋታ ነው ብዬ አስቤ ነበር፤ ነገር ግን ፍቅርሽ የተረጋጋ እና በፀጥታ ውስጥ ያለ የእናት ፍቅር ነው” - ማቲዮ፣ ብራዚል
ስለ እናት ብዙ ተብሏል፣ ብዙም ተጽፏል፤ ነገር ግን እነዚህ ደብዳቤዎች የቃላት ድርድር ብቻ አይደሉም። የእውነት የተኖሩ የእናትነትን የፍቅር ማሳያ ታሪኮች ናቸው።
የእናት ፍቅር ተነግሮ አያልቅምና እርስዎም ስለ እናት ፍቅር ያለዎትን ሐሳብዎን እና ስሜትዎን በሐሳብ መስጫው ሳጥን ውስጥ ያስቀምጡልን።
መልካም የእናቶች ቀን!
በሴራን ታደሰ