በምሥራቅ አፍሪካ የሚስተዋለውን የሽብርተኝነት አደጋና የግጭት መበራከት የቀጣናው አገራት በጋራ እልባት ሊያበጁለት እንደሚገባ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የፀጥታና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ገለጹ።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚፈጠር ግጭት እና አለመረጋጋቶች ለሽብርተኞች እንቅስቃሴ ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።
በመሆኑም በቀጣናው በስፋት የሚስተዋለውን ግጭት እና አለመረጋጋት በዘላቂነት መፍታት የአገራቱ ቀዳሚ ሥራ መሆን እንዳለበት ይታመናል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የፀጥታና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ፤ አልሻባብና ሌሎችም የሽብር ቡድኖች ቀጣናውን ለማወክ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣናው ለሚስተዋለው የሽብርተኞች እንቅስቃሴ አንዱ ምክንያት በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚፈጠር የእርስ በርስ ግጭቶችና አለመረጋጋት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የግጭት መበራከት ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት የሽብርተኞችን አደጋ በጋራ መመከትና ዘላቂ መፈትሄ መሻት ይገባል ነው ያሉት።
ለአካባቢው አለመረጋጋት ሌላኛው ምክንያት የጂኦ-ፖለቲካ ሽኩቻ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ የቀጣናው አገራት ለችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ ለማምጣት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የህዝቦች ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ ሁሉም አባል አገራት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ኢጋድ ዓለም አቀፍ ህጎችና ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግን ጨምሮ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።