ባለፉት 4 ወራት ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰዋል

2 Yrs Ago
ባለፉት 4 ወራት ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰዋል
ሌሊሴ ነሚ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር

 ባለፉት አራት ወራት ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰሳቸውን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ወደ አገር ቤት የሚመጡ አንድ ሚሊየን ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያዩበት መድረክ በማዘጋጀትም ሀገሪቱ አዳዲስ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ካፒታል እንድታገኝ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፥ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ጥሪ ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያዩባቸው መድረኮች እየተዘጋጁ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

መድረኮቹ በኢትዮጵያ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ አቅሞችን ማየት የሚያስችሉ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ዳያስፖራው መዋዕለ ንዋዩን ለማውጣትና በአገሩ የሚያፈስበትን አማራጮች ለመሳተፍ ሲመጣ የሚስተናገድበት ራሱን የቻለ ዴስክ መክፈቱንም ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው በመምጣት በአገር በቀል ኢንቨስትመንቶች ውስጥ እገዛ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው ያልተነኩ የአገሪቷን የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የውጭ ባለሃብቶችን ኢንቨስትመንቶችና ተያያዥ ስራዎች እንዲጎበኝ ይደረጋልም ብለዋል።

ወደ አገር ቤት ያልገቡ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያዩ መንገዶች እያሳወቁ እንደሚገኙም ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

ለዚህ ስኬትም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከዳያስፖራ ኤጀንሲና ከክልሎች ኢንቨስትመንት ቢሮዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአማራና በአፋር ክልሎች በነበረው ጦርነት ስራ አቁመው የነበሩ የኢንቨስትመንት መስኮችን በማስተባበር ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top