የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ" መርሐ ግብርን ያጠናቀቁና ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረላቸው 13 ሺህ 527 ወጣቶችን አስመርቀዋል።
ይህንን አስመልክተው ከንቲባዋ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት፤ ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሐ ግብር በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች ወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋ ወጣቶች በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከጀመራቸው ስትራቴጂዎች አንደኛው መሆኑንም ከንቲባዋ አመላክተዋል።
"የከተማችን ወጣቶች ክህሎት በስራ ላይ ልምምድ ብቻ የሚያበቃ ባለመሆኑ ወደ ስራ ስትገቡ ይበልጥ ራሳችሁን በብቃት እንድታሳድጉ፣ስራን ከማማረጥ በመውጣት እና ጠንካራ የስራ ባህልን በማዳበር በተፈጠርላችሁ የስራ እድል በሙሉ እንድትጠቀሙ አደራ ማለት እወዳለሁ" ብለዋል።
በቀጣይ 15 ሺህ የከተማዋ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 3ኛ ዙር ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ መርሐ ግብር በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን የገለፁት ከንቲባዋ፤በመሆኑም የከተማዋ ወጣቶች በዚህ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ከንቲባዋ በወጣቶቹ የስራ ላይ ልምምድ ወቅት የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን የዓለም ባንክ ጨምሮ ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስተዋፅዖ ያደረጉ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የከተማዋ የስራና ክህሎት ቢሮ፣ ባለሐብቶች እንዲሁም ፕሮግራሙን ላሳኩ በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።