ከባየር ሙኒክ ደጋፊነት እስከ አሠልጣኝነት - የጁሊያን ናግልስማን የስኬት ምሥጢሮች

2 Days Ago 241
ከባየር ሙኒክ ደጋፊነት እስከ አሠልጣኝነት - የጁሊያን ናግልስማን የስኬት ምሥጢሮች

በእግር ኳስ ታክቲክ ሊቅ እንደሆነ ይነገርለታል። በአማካይ ስፍራ የተጫዋቾችን ቁጥር በማብዛት ጨዋታን መቆጣጠር፤ አጥቅቶ በመጫወት ማሸነፍ የሚረዳ ፍልስፍና ይከተላል። የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ከባየር ሙኒክ ጋር አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። በጀርመን በዘመኑ ካሉ ምርጥ አሠልጣኞች መካከል አንዱ ነው። 

በእግር ኳስ ተጫዋችነት ትልቅ ስኬት ለመድረስ የነበረው ህልም ባጋጠመው ጉዳት በ20 ዓመቱ ጨማውን ለመስቀል ቢገደድም ፊቱን ወደ አሠልጣኝነት በማዞር ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ወጣቱ አሠልጣኝ እያሳየ ባለው ብቃት “ትንሹ ሞሪኒሆ” የሚል ቅፅል ስም አስገኝቶለታል - የአሁኑ የጀርመን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን። 

የተወለደው እ.አ.አ በ1987 በደቡባዊ ምእራብ የባቫሪያ ከተማ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ላንድስበርግ ከተማ ውስጥ ነው። 

ለባየር ሙኒክ ክለብ ጥልቅ ፍቅር ስለነበረው በሕፃንነቱ የክለቡን ማሊያ ለብሶ ሳያወልቀው ይተኛ ነበር። በትውልድ አከባቢው ለታዳጊ ክለብ ተጫውቶ ዋንጫዎችን አሸንፏል። 

በተጫዋችነት ሕይወቱም ያጋጠመው ጉዳት ከ4 ወራት በላይ ከሜዳ ስላራቀው በ20 ዓመቱ ጫማውን ለመስቀል ተገዷል። 

የኦግስበርግ ሁለተኛ ቡድን አሠልጣኝ የነበሩበት አሠልጣኝ ቶማስ ቱኼል የሌሎች ታጋጣሚ ክለቦችን ድክመት እና ጥንካሬዎችን አጥንቶ እንዲያመጣ ኃላፊት ሰጥተውት መስራቱ ወደ እግር ኳስ አሠልጣኝነት እንዲገባ ምክንያት እንደሆነው ይናገራል። 

አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ እና አሠልጣኝ ቶማስ ቱኼል ለእግር ኳስ አሠልጣኝነቱ አርአያዎቹ መሆናቸውን የሚናገረው ወጣቱ አሠልጣኝ፣ እ.አ.አ በ2010 በሆፍንሄም እግር ኳስ አካዳሚ ውስጥ የአሠልጣኝነት ሕይወት አንድ ብሎ ጀመረ።

 

እ.አ.አ በ2015/2016 በቡንደስ ሊጋው ወራጅ ቀጠና (17ኛው) ደረጃ ይገኝ የነበረው ሆፍንሄም በወጣቱ አሠልጣኝ ብርቱ ሥራ በዓመቱ መጨረሻ 3ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ቻለ። 

ክለቡ ከወራጅ ቀጣና አውጥቶ ለአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ እንዲደርስ ማድረግ በመቻሉ በጀርመን የዓመቱ ኮከብ አሠልጣኝ ሽልማትን አሸንፏል። 

እ.አ.አ በ2019 ከሆፍንሄም ወደ አር ቢ ሌብዚሽ በመሔድ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እስከ ግማሽ ፍፃሜ በማድረስ ታሪክ ሠርቷል። በሕፃንነቱ የባየር ሙኒክ ደጋፊ ሆኖ ያደገው አሠልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን እ.አ.አ በ2021 በ25 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ (በአሠልጣኞች ዝውውር ታሪክ ከፍተኛ ዋጋ) ባየር ሙኒክን ተቀላቀለ። 

የባየር ሙኒክ አሠልጣኝ ሆኖ በተሾመበት ዓመት ክለቡ የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ በተከታታይ 10ኛ ጊዜ እንዲያሸንፍ በማድረግ የልጅነት ሕልሙን አሳክቷል። 

ወጣቱ አሠልጣኝ በሀገሪቱ ተፅእኖ ፈጣሪ የእግር ኳስ አሠልጣኞች መካከል ስሙ ተጠቃሽ ሆኗል።

 

በጥልቀት ማሰብ የሚችል፣ ተለዋዋጭ የአጨዋወት ሥልት እና ታክቲክ የሚተገብር ውጤታማ አሠልጣኝ መሆኑን ባለሙያዎች ይመሰክሩለታል። 

በወጣትነቱ ስለእግር ኳስ ያለው አስገራሚ እውቀት፣ በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል። ለተጫዋቾች ምሳሌ የሚሆን መልካም  ስብዕና ያለው እና የበሰሉ ፋጣን ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ በበርካቶች ይሁንታን አስገኝቶለታል። 

እ.አ.አ ከ2023 መስከረም ጀምሮ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ በመሆን እየሠራ የሚገኘው ጁሊያን ናግልስማን፣ በቅርብ ዓመታት በጀርመን ተፅዕኖ ፈጣሪ የእግር ኳስ አሠልጣኞች መካከል አንዱ መሆን ችሏል። ናግልስማን በተጫዋችነት ዘመኑ የመሐል ተከላከይ ወይም አማካይ ተጫዋች እንደነበረ ይናገራል። 

ከመከላከል ይልቅ በመሐል ሜዳ በኳስ ቁጥጥር በልጦ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማመቻቸት ችሎታ እንደነበረው ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

 

ያመነበትን ነገር በእውቀት እና በድፍረት መወሰን መቻሉ አሁን ላለበት አድርሶታል። በመሐል ሜዳ ኳስን ተቆጣጥሮ በፍጥነት መጫወት የሚከተለው የአጨዋወት ፍልስፍናው በበርካቶች ይወደድለታል። ከተጫዋቾች ጋር ያለው ግንኙነት ጠንከራ እና ተፅእኖ መፍጠር የሚችል ቡድን እንዲገነባ አስችሎታል። 

ጀርመን ራሷ የዘጋጀችውን የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ማሸነፍ ባትችልም  በአጨዋወቱ ግን የጀርመናውን ዳጋፊዎችን ልብ ማሸነፍ ችሏል። በተለይም በ28 ዓመቱ ሆፍንሄምን ከወራጅ ቀጣና በማውጣት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እንዲሳተፍ ማድረግ መቻሉ፣ ሌብዚሽን በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ እንዲገባ ማድረጉ፣ በ2021/22 የውድደር ዘመን 3 ጨዋታዎች እየቀሩት ከባየር ሙኒክ ጋር የቡንደስሊጋ ዋንጫ ማሸነፉ፣ የጀርመን ሱፐር ካፕ ዋንጫን 2 ጊዜ  ማሸነፉ ጀርመናውያያን ተስፋ እንዲጥሉበት አድርጓል። 

እግር ኳስ 30 በመቶ ታክቲክ 70 በመቶ የቡድን ሥራ መሆኑን የሚናገረው አሠልጣኙ ተጫዋቾች ሲያሸንፉ ብቻ ሳይሆን ጉዳትም ሆነ ሽንፈት ሲያጋጥማቸው  የሥነ ልቦና ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎች አስፈላጊ እንደሆነም ይገል። የተጫዋቾች ሥነልቦናዊ ዝግጁነት ከፍ ማለት ሁሌም ለመሻሻል ለመለወጥ ያነሳሳሉ፤ ራሳቸውን ለማሻሻል ሁሌም ጥረት ያደርጋሉ ይላል። 

ጀርመናዊ አሠልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን - የአዲሱ የእግር ኳሱ የታክቲክ ሊቅ፣ የትልቅ ስብእና ባለቤት፣ እምቅ ችሎታ፣ ጠንካራ የራስ መተማመንን ይዞ በጀርመን ብሔራዊ ቡድን ወደፊት አዲስ ታሪክ እንደሚሠራ ይጠበቃል። 

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top