ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ ፍትሃዊ ነው፦ የሕግ ባለሙያ

20 Hrs Ago 91
ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ ፍትሃዊ ነው፦ የሕግ ባለሙያ
ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ ፍትሃዊ ነው ሲሉ የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ ገለጹ፡፡
 
ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የባሕር በር የነበራት ኢትዮጵያ የወጭና ገቢ ንግዷን በነበሯት ወደቦች ታስተናግድ ነበር። ይህም በኢኮኖሚዋ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው።
 
ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባሕር በር የሌላት ወይም ወደብ አልባ ሀገር ሆና ወደብ ባላቸው ሀገራት ላይ የወጭና ገቢ ንግዷን እያስተናገደች ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ታደርጋለች።
 
የሕግ ባለሙያና ጠበቃ የሆኑት አቶ አንዱዓለም በእውቀቱ ኢትዮጵያ እና የባሕር በርን በተመለከተ በዛሬው የኢቲቪ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" መሰናዶ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አሁን ላይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ መሆኑን እና የዓለም ሀገራትም በዚህ መስማማታቸውን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
 
የባሕር በር ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ መሆኑ ተገቢ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ ኢትዮጵያ ያነሳችው ጥያቄ ፍትሃዊ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡
 
ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በቀጣናው ካላት ሚና እና ከህልውናዋ አንጻር የባሕር በር ጥያቄዋ ፍትሃዊ እንደሆነ ይገልጻሉ።
 
በብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር መንግስት እና አጀንዳውን ያልረሳ ህዝብ ሲኖር በየትኛውም ጊዜ ጉዳዩን ማንሳት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡
 
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አመራርና ልማት ጥናት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ታምራት ደስታ በበኩላቸው፤ የባሕር በር ተደራሽ መሆን የምትሻው ኢትዮጵያ ይህንን በሰላማዊ መንገድ እውን የማድረግ ፍላጎት አላት ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ገንዘብ ለተለያዩ ልማቶች በማዋል ኢኮኖሚዋን ማሳደግ እንደምትችል ገልጸው፤ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ የርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ባለቤት እና ከባሕር በር በቅርብ ርቀት የምትገኝ ሀገር ሆና የባሕር በር ባለቤትነት ተነፍጋለች ይላሉ።
 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን እያቀረበ ይገኛል፤ በመሆኑም ይህ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ነው አቶ ታምራት የገለጹት።
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top