የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ነፃ እስከሚወጡ ድረስ አኗኗራቸውን፣ ባህላቸውን፣ እሴት እና እሳቤያቸውን የሚያንፀበርቁበት የራሳቸው የሆነ ሰንደቅ ዓለማ እንዳልነበራቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ከአህጉር አፍሪካ በቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀች፣ የጣሊያን ወራሪ ኃይሎችን አንበርክካ የመለሰች አፍሪካዊት ሀገር - ኢትዮጵያ ነች።
ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ የአፍሪካ ሀገራትም የነፃነት እና የአልበገር ባይነት ምልክት የሆነውን፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማን መሠረት አድርገው የራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማ እንደቀረፁ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት እና ምርምር ማዕከል መምህር እና ተመራመሪ ዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ፤ ነፃነታቸውን የተጎናፀፉ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ የነፃነት ትግል አርማ አድርገውታል ይላሉ::
ዶ/ር ሳሙኤል ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ሰንደቅ የማታገያ መንፈስም አድርገው እንደተጠቀሙበት ነው የተናገሩት::
ኢትዮጵያዊያን አይነኬ የሚመስለውን የነጮችን የበላይነት በአንድነት ለመመከት ባደረጉት ተጋድሎ ድል በመቀዳጀታቸው በመላው ዓለም የጥቁር ሕዝቦችን አንገት ቀና ማድረግ ችለዋል።
ጣሊያን በኢትዮጵያዊያን ሽንፈትን ተከናንበው መውጣታቸው፣ የኢትዮጵያን ተፈላጊነት በዓለም መድረክ ከፍ አድርጓል ይላሉ ዶክተር ሳሙኤል።
ለዚህም ነው ሰንደቅ ዓላማችን በመላው አፍሪካዊያን ብሎም በጥቁሮች ዘንድ እንደ ትልቅ የእኩልነት፣ የነፃነት እና የተጋድሎ አርማ ተደርጎ ሊወሰድ የቻለው።
ይህንን የተረዱ አፍሪካውያንም የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ምልክት አድርገው መጠቀም መቻላቸውን ዶ/ር ሳሙዔል ተፈራ የገለፁት።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝምን ንቅናቄን በማፋጠን፣ አፍሪካዊያን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመደገፍ የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሠረት በቀዳሚነት ጉልህ አሻራዋን አስቀምጣለች:: በዓለም መድረክም አፍሪካዊ አጀንዳዎችን በማንሣት እስከዛሬም የዘለቀች ታላቅ ሀገር እና መንግሥት ያላት ሀገር ናት።
የቅኝ ግዛት ቀንበር መሸከም ያንገሸገሻቸው ሁሉ የኢትዮጵያን የድል ፋና ተከትለው ትግል ለማድረግ እንዲያስችላቸው የኢትዮጵያ ንጉሥ ቀዳማይ አፄ ኃ/ሥላሴ ለአፍሪካዊያን ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
በሂደትም በርካታ አፍሪካዊያን የሰንደቅ ዓላማቸውን ቀለም ከኢትዮጵያ በመውሰድ ጀግንነትን እና ጀብደኝነትን ወርሰዋል።
ጋና፣ ሴኔጋል፣ ማሊ፣ ካሜሩን፣ ጊኒ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቶጎ፣ ሞሪሺዬስ፣ ዚምባቡዌ ያሉ ሀገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለም የሚጋሩ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ምልክት የሆኑ ቀለሞች በአፍሪካ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዓለም ሀገራት የነበሩ ለነፃነት እና እኩልነት የሚታገሉ ፓን አፍሪካን ድርጅቶች፣ የራስ ተፈሪያን ንቅናቄ፣ ዓለም አቀፍ የኔግሮ ኅብረት ንቅናቄ እና የአፍሪካ ማኅበረሰብ ሊግን የመሳሰሉ ድርጅቶች አርማውን ሲጠቀሙበት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በምሥራቅ አውሮፓ ሉቲኒያ እና ሄይቲ፣ በአሜሪካ ካሪቢያን ውስጥ የፓን አፍሪካ ንቅናቄን የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች መፈጠሩን ዶክተር ሳሙኤል አንሥተዋል።
አፍሪካዊን የሰንደቅ ዓለማውን አርማ ቅኝ ግዛትን እና ቅኝ ገዢዎችን እንደመዋጊያ ምልክት አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበረ ዶ/ር ሳሙኤል አስታውሰዋል::
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲያዩ ከባርነት ነፃ የመውጣት፣ የጥቁር ሕዝብ መንግሥት እና የመሪነት ስሜት ለነፃነት አብቅቷቸዋል::
በመሐመድ ፊጣሞ