ዓለም አቀፍ የማይበገር ቱሪዝም ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በፌብሩዋሪ 17 ቀን 2023 ዓ.ም የተከበረ ሲሆን፣ ሀገራት ወደፊት የሚፈጠረውን ችግር መቋቋም የሚችል ጠንካራ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲገነቡ በማለም የተጀመረ ነው።
ቱሪዝም ለብዙዎቹ ታዳጊ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ሀገራት ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ቱሪዝም የውጭ ምንዛሬ ገቢ እና ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ዘርፍ ሲሆን፤ በመላው ዓለም በተለይም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሴቶች እና ወጣቶች ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው።
አንዳንድ አነስተኛ ደሴቶች እና ታዳጊ ሀገራት 20 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርታቸው ከቱሪዝም የሚገኝ ነው።

ቱሪዝም ሰዎችን ከተፈጥሮ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ዘላቂ እና የተጠናከረ ቱሪዝምን ለመፍጠር ጥበቃ ያስፈልገዋል።
ለዚህም ነው ዘርፉን ለማነቃቃት እና ለመደገፍ በማሰብ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የማይበገር ቱሪዝም ቀን በማለት እ.አ.አ በፌብሩዋሪ 17 በመላው ዓለም መከበር የጀመረው።
ዓለም አቀፍ የማይበገር ቱሪዝም ቀን ሲከበር የተሻለ እና ጠንካራ ቱሪዝምን ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመላክታል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የታወጀው ይህ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እና ድንገተኛ ክስተቶችን ለመፍታት የሚያስችል የቱሪዝም ልማት እንዲስፋፋ ያለው ሚናም የጎላ ነው።
ኢትዮጵያም ትኩረት ሰጥታ እየሠራችባቸው ካሉ የልማት ሥራዎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ ሲሆን፤ በዘርፉም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።
ሀገሪቱ በዘርፉ ሰፋፊ ሥራዎችን በመሥራት፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስፋፋት፣ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ገንዘብ እየቀየረች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና በታሪካዊ ሀብቷ ለቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ ሀገር ስትሆን፤ ይህን ሀብት በመጠቀም የቱሪስት መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል።

ከነዚህ መካከል የገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለሸገር እንዲሁም ገበታ ለትውልድ ሥራዎች በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በርካታ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ቅርሶች እንዲሁም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገባቸውም አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ 10 የሚዳሰሱ ቅርሶችን እና 5 የማይዳሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ አስመዝግባለች።

ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ እና የታሪክ ሀብት ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ ብትቆይም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ መዳረሻዎችን በማስፋት፣ የቱሪስቶችን ቆይታ በማስረዘም በቱሪዝሙ የተለያዩ ጥቅሞችን እያገኘበት ይገኛል።
ከዚህ ጎን ለጎን፥ የቱሪዝም ዘርፉን የማስተዋወቅ ሥራ በሰፊው መሠራት እንዳለበት የዘርፉ ባለሞያዎች ይመክራሉ።
በሜሮን ንብረት