ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደ ኅብረቱ መቀመጫ ሀገር የሚጠበቅባትን አከናውናለች። ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በመልዕክታቸው::
አቀባበሉ፣ መስተንግዶውና መርሐ ግብሮቹ እንግዶቻችንን ያስደመመ ነበር።
እንግዶቿ የማይረሳ ትውስታ፣ የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች። በዚህ የተነሣ የቆይታ ጊዜያቸውን ያራዘሙ እንግዶች ብዙ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዓላማዎች እና መርሖች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት በጉባኤው ዝግጅትና መስተንግዶ በተግባር አሳይታለች።
የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ብዙዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
አዘጋጅ ኮሚቴው፣ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ የፕሮቶኮል ባለሞያዎች፣ የቴሌና የመብራት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የትራፊክ ፖሊሶች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብና የሰርከስ አባላት፣ ሆቴሎች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፣ የጽዳት ባለሞያዎች፣ እንደ አንድ ልብ ሰሚ፣ እንደ አንድ አካል ፈጻሚ ሆነው ተሠርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ለእንግዶቹ ተገቢውን ክብርና መስተንግዶ በመስጠት፣ መንገዶች ሲዘጉ በትዕግሥት በመጠባበቅ፣ ለጉባኤው ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጓል።
ለሁላችሁም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።
ሁላችንም በሀገር ፍቅር ስሜት በሥርዓት እና በዲሲፕሊን በመሥራታችን እንግዶቻችንን አስደምመናል።
የሀገራችንን ከፍታ አሳይተናል። ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑት የሚዲያ ሰዎች መልካም ገጽታችንን ለዓለም አሳይተዋል። ከዐሥር ሺ ዎች የሚልቁት እንግዶች እየበለጸገች ስለምትገኘው ሀገራችን ምስክሮች ሆነዋል።
ይህ ትብብራችንና ለሀገራችን ስኬት ያለን ቁርጠኝነት፣ ከጉባኤው በኋላም እንደሚቀጥል አምናለሁ።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መሆንዋ በዐለት ላይ እስኪጻፍ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል።