ባለፉት ሥድስት ዓመታት የምርምር ተቋማትን በመጠቀም የስንዴ ምርታማነት ላይ በትኩረት በመሰራቱ ተጨባጭ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ ጉባዔን አስመልክቶ የፓርቲው የስካሁን ጉዞ ምን ይመስላል በሚል ኢቲቪ ከግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አካሂዷል።
ባለፉት ሥድስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ያጋሩት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ በስንዴ ልማት ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በመውጣት የምርምር ተቋማትን በመጠቀም በዕውቀት እና በእቅድ በተሰራው ስራ እመርታዊ ለውጥ መገኘቱን ተናግረዋል።
በዚህም ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ወጥተን ወደ ውጭ እስከመላክ መድረሳችን በተግብር የታየ ውጤት ነው ብለዋል።
የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በተከናወነ ስራ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ በማስገባትና አርሶ አደሩ እንዲጠቀምባቸው በማድረግ 25 በመቶ በመኸር የሚታረሰው መሬት ከበሬ እርሻ መላቀቁን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
"ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው የብልጽግና ሁለተኛ ጉባኤ፤ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ ስራዎችን ወደ ባሕል የመቀየርና የማፅናት እንዲሁም የተጀመሩትን የማስቀጠል ተግባርን ማዕከል ያደረገ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ማንኛውም ስራ ከሀሳብ በመነሳት ወደ ተግባር የሚሄድ በመሆኑ ሀሳቡን ተቀብሎ ወደ ዕቅድ የማምጣት እና ወደ ተግባር የመለወጥ ስራ እንደሚያስፈለግ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ ሀሳቡን ተግብረን የማይቻል የሚመስሉ ነገሮችን ተችለው መመልከት እና ተጠቃሚ መሆን ችለናል ብልዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ዳር ተመልካች የነበሩትን እና በፖለቲካ የተገለሉትን አካላት በማካተት ሀገራዊ ውሳኔዎችን ጭምር አብረው እንዲወስኑ ማድረግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም እኩል ተሳታፊ በመሆን ሁሉም አካባቢውን ለማልማት በተፈጠረለት ዕድል ለኢትዮጵያ የተሻለ እድገት ትልቅ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ ገልፀዋል።