የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዲሳካ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የቪአይፒ (VIP) ፕሮቶኮል አጃቢዎች እና የአሽከርካሪዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ኮሚሽነር ጀነራሉ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ተቋሙ የታጠቃቸው ድሮኖችና ሌሎች ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ እንደሚውሉ ጠቁመዋል።
የሰው ኃይሉን በሀገር ውስጥ፣ በቻይና እና በተባበሩት ዐረብ ኢሚሬት ዱባይ በማስልጠን እና የፀጥታ ሥራውን በማዘመን ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በስልጠና ያገኛችሁትን ዕውቀትና ክህሎት በተግባር ላይ በማዋል፣ በጥብቅ ዲሲፕሊንና በቅንጅት በመስራት አምባሳደር ሆናችሁ የሀገራችንን ገፅታ የበለጠ ከፍ በማድረግ የሕብረቱ ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን መሥራት ይጠበቅባችኋል በማለት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ለተመራቂዎች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በኮልፌ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ስልጠና የወሰዱት የVIP ፕሮቶኮል አጃቢዎች እና አሽከርካሪዎች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ቤተመንግስት፣ ከባህልና ቱሪዝም፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የራይድ ትራንስፖርት እና የመኪና አከራይ ድርጅቶችን ጨምሮ ከ55 ተቋማት የተውጣጡ መሆናቸው ታውቋል።