በትግራይ ክልል ዕዳጋ ሐሙስና መቐለ ከተማ በሚገኙ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና ያጠናቀቁ 3 ሺህ 502 የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል እያከናወነ ባለው የመልሶ ማቋቋም አተገባበር፣ ያገጠሙ ተግዳሮቶችና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በአክሱም ከተማ ምክክር አካሂዷል፡፡
በክልሉ ዕዳጋ ሐሙስና መቐለ ከተማ በሚገኙ ማዕከላት የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ያጠናቀቁ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ መጀመሩ በመድረኩ ተገልጿል።
በዚህም የኮሚሽኑን እቅድ፣ የዲሞብላይዜሽን አተገባበር ሂደት ያቀረቡት ሌተናል ኮሌኔል ጎሳዬ ጥላሁን፤ስከ ዛሬ ባለው ክንውን ኮሚሽኑ በሁለቱ ማዕከላት 4 ሺህ 963 የቀድሞ ታጣቂዎች ተቀብሎ ስልጠና መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም 3 ሺህ 502 የሚሆኑት ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደ ማህበረሰቡ መላቀላቸውን ጠቅሰው፤1 ሺህ 461 የሚሆኑት ደግሞ በማዕከላቱ የተሃድሶ ስልጠናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው እየተሳተፉ ካሉት 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያው በበኩላቸው፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን የዲሞብላይዜዝ የማድረግና መልሶ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ በቀጣይ በዓድዋ ማዕከል እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም ስኬት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ያሉ ሲሆን፤ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ምክትል ኮሚሽነርሩ ጠይቀዋል፡፡
የማዕከላዊ ትግራይ አርበኞች ኮሚሽን ምክትል ኃላፊ ኪሮስ ሃይለ በበኩላቸው፤ የተጀመረውን የመልሶ ማቋቋም ትግበራ ከኮሚሽኑና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በውጤት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ማለታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
በምክክሩ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ የኮሚሽኑ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ ከማዕከላዊ ትግራይ ዞን፣ ከዓድዋ እና ከአክሱም ከተማ እንዲሁም ከዓድዋ ወረዳ የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡