ዛሬ ምሽት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የመሬት ንዝረት ለ18 ሰከንድ ያህል መቆየቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ ፊዚክስ ስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም አስታውቋል፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤልያስ ሌዊ በመዲናዋ የተከሰተው የመሬት ንዝረት በአዋሽ ፈንታሌ ተራራ አካባቢ በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ሞገድ አማካይነት የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በአዲስ አበባ የተከሰተው የመሬት ንዝረት መሆኑን አውቆ፤ የእለተ እለት እንቅስቃሴውን በተረጋጋ መንገድ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በፈንታሌ ተራራ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.9 ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን ዶ/ር ኤልያስ ሌዊ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል።
በፈንታሌ ተራራ አካባቢ ከምሽቱ 2 ሰአት ከአስር ደቂቃ ከሶስት ሰከንድ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሞገዱ በመሬት ውስጥ ተጉዞ አዲስ አበባ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ንዝረት መፍጠሩንም ነው ዶ/ር ኤልያስ ያስረዱት።
አሁን የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተበት የፈንታሌ አካባቢ ለመሬት መንቀጥቀጥ የተጋለጠ አካባቢ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ኤልያስ፤ አካባቢው ብዙ ነዋሪ የሌለበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ተቋሙ ተጨማሪ መረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት ዶ/ር ኤልያስ በቀጣይ ዝርዝር መረጃዎችን ተቋሙ እንደሚያቀርብ እና እንዲህ ያለ አደጋ ሲያጋጥም የቤት ቋሚዎች በተለይ ኮንዶሚኒየም ህንጻ ላይ ያሉ ሰዎች ኮለኖች አካባቢ መጠጋት፣ ጠረጴዛ ስር መግባት፣ ሊፍት አለመጠቀም፣ ውጪ ላይ የመብራትና መሰል ምሶሶዎችን አለመጠጋት እንደሚያስፈልግ ዳይሬክተሩ መክረዋል።
በጌታቸው ባልቻ