የወንጀል ቅጣትን ሊያስቀይሩ ወይም ሊያስቀሩ ሚችሉ ሕጋዊ አማራጮች የትኞቹ ናቸው? ይቅርታ፣ ምህረት፣ ገደብ እና መሰየም እንዴት ይፈቀዳሉ? ውጤታቸውስ ምንድን ነው?
ሀ.ይቅርታ
የይቅርታ ጥያቄ አንድ ፍርድ በሙሉ ወይም በከፊል ቀሪ እንዲሆን የቅጣቱ አፈፃፀምና ዓይነት በቀላል ሁኔታ እንዲፈፀም ለማስደረግ በሚቀርብ ጥያቄ መሰረት የሚሰጥ ውሳኔ ውጤት ነው።
ጥያቄው በተቀጪ፣ በትዳር አጋር፣ በቅርብ ዘመዶች፣ በወኪሉ ወይም በጠበቃው አማካኝነት ወይም ደግሞ በማረሚያ ቤቱ በኩል ሊቀርብ ይችላል። ይቅርታውን የጠየቀው የማረሚያ ቤቱ ከሆነም የይቅርታ ጥያቄው በቀረበ በ15 ቀናት ውስጥ ተቀጪው ይቅርታውን የማይፈልገው ከሆነ በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት። ከአቅም በላይ ችግር ካላጋጠመው በስተቀር ዝም ማለቱ ይቅርታውን እንደተቀበለ ያስቆጥረዋል።
የይቅርታ መርማሪ ቦርዱም ጥያቄውን መርምሮ ይቅርታው በቅድመ ሁኔታ ወይም ያለ ቅድመ ሁኔታ መሰጠት እንዳለበት ወይም ቅጣቱ በሙሉ በከፊል ወይም በቀላል መንገድ መፈፀም እንዳለበት ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል። በአዋጁ አንቀፅ 10 መሰረት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በቦርዱ የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ወይም በራሱ ምክንያት ይቅርታ መስጠት ወይም የመከልከል ስልጣን ያለው ሲሆን፤ በቅድመ ሁኔታ ይቅርታ ተደርጎላቸው ቅድመ ሁኔታውን ያላሟሉትን ደግሞ በቦርዱ የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ይቅርታውን የመሰረዝ ሥልጣን አለው።
ለ. ምህረት
በወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 230 መሠረት በሕግ ምህረት እንደማይሰጥባቸው ካልተደነገጉ በስተቀር በጅምላ ለአንድ ዓይነት ወንጀሎች ወይም በተመሳሳይ ደረጃ ለሚገኙ ወንጀሎች በገደብ ወይም ያለምንም ገደብ አግባብ ባለው አካል ጠቅላላ ምህረት ሊሰጥ ይችላል። ይቅርታ ግለሰባዊ እና ከቅጣት ውሳኔ በኋላ በተቀጪው ፍላጎትና ፍቃድ የሚጠየቅ ሲሆን፤ ምህረት በጥያቄ የሚሰጥ ካለመሆኑም በተጨማሪ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በአጠቃላይ የሚሰጥ ነው። በተጨማሪም ከነጭራሹ የወንጀል ክስ እንዳይጀመር የተጀመረውም እንዳይቀጥል ቅጣት ተወስኖ ከሆነም ቅጣቱ የሚያስከትለው የወንጀል ውጤት እንዳልነበረ ተቆጥሮ ከወንጀለኞች መዝገብ ላይ እንዲሰረዝ ያደርጋል። ይቅርታ ግን ቅጣትን ሊያስቀር፣ ሊያስቀንስ ወይም በአነስተኛ መልኩ ሊለውጥ የሚችል ቢሆንም፤ ከምህረት በተቃራኒ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 229(2) ላይ በተቀጪው ላይ የተወሰነው ፍርድና ውጤቱ በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ የሚኖር ነው። ይቅርታ እና ምህረት ለተበዳዩ በፍትሐ ብሔር ሊከፈል የሚችለውን ካሳ የማያስቀሩ ሲሆኑ፤ ተቃራኒ ትዕዛዝ ካልተሰጠ በስተቀር ለመንግሥት የሚከፈል ኪሳራ በይቅርታ ወይም በምህረት ቀሪ ይሆናል።
ሐ. ቅጣትን መገደብ
በወንጀል ሕግ አንቀፅ 190 ፍርድ ቤቶች ለጥፋቱ መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች በማገናዝብ የተወሰነውን ቅጣት መገደቡ ወንጀለኛውን ፀባዩን ለማረም እና ወደ መደበኛ ኑሮው ለመመለስ ጠቃሚ መሆኑን ካረጋገጡ ቅጣቶችን በሁለት መልኩ ሊገድቡ ይችላሉ።
የመጀመሪያው በመቀጮ፣ በግዴታ ሥራ ወይም ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ለሚያስቀጡ ጥፋቶች ፍርድ ቤቱ የወንጀለኛውን ጥፋተኝነት ካረጋገጠ በኋላ ወደፊት ሊታረም እና እምነት ሊጣልበት የሚችል ሆኖ ሲያገኘው ቅጣት ከመወሰኑ በፊት የሚወስነው የመፈተኛ ጊዜ ይሰጠዋል። ፈተናው ፍርድ ቤቱ እንደገመተው መልካም ውጤት ካስገኘ በወ/ሕ/አ 191 መሰረት ፍርዱ እንዳልነበረ ተደርጎ ይቆጠራል።
ሁለተኛው የገደብ ዓይነት ደግሞ በወ/ሕ/አ 192 መሰረት ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ከወሰነ በኋላ ለወንጀለኛው ፀባይ መሻሻል አንድ ፅኑ ማስጠንቀቂያ ብቻ በቂ መሆኑን ሲያምንበት ቅጣቱን ከመፈፀም ለተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ የማያዝበት ነው። የተወሰነው የፈተና ጊዜ ውጤታማ ከሆነ ቅጣቱ አይፈፀምም፤ ሆኖም ፍርዱና ውጤቱ በወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ይኖራል። ሆኖም ግን ሁሉም ወንጀለኞች ቅጣት ሊገደብላቸው አይችልም። በወ/ሕ/አ 194 ተደጋጋሚ ወንጀለኞች አስቀድሞ በፅኑ እስራት ወይም ከሦስት ዓመት በሚበልጥ ቀላል እስራት ከተቀጡ እና በተከሰሱበት ወንጀልም ከእነዚህ ቅጣቶች አንዱ የሚወሰንባቸው ከሆነ ቅጣቱ ሊገደብ አይችልም። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ባይቀጡም በተከሰሱበት ወንጀል ከአምስት ዓመት የበለጠ ፅኑ እስራት የሚያስፈርድ ቅጣት ከተቀጡ ቅጣቱ አይታገድም። ቅጣቱ ከመታገዱ በፊት ከላይ የተጠቀሰውን ቅጣት የሚያስከትል ወንጀል መፈፀሙ ከተደረሰበት፣ ቅጣት ከታገደለት በኋላም አስቦ አንድ ወንጀል ከፈፀመ፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠው የፈተና ጊዜ መልካም ውጤት እንደማያስገኝ ከተረዳው ቅጣቱ አይታገድም። ከሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች በተጨማሪም ቅጣት ተገድቦ የሚሰጠው የፈተና ጊዜ ከሁለት ዓመት ያነሰ ወይም ከአምስት ዓመት የበለጠ መሆን የለበትም።
መ. በአመክሮ መፈታት
በአመክሮ መፈታት ማለት ተቀጪው የተወሰነበትን ቅጣት ቢያንስ ሦስት ሁለተኛውን ካጠናቀቀ በኋላ የተቀጪውን ፀባይ ለማሻሻያና ወደ መደበኛ ኑሮው መመለሻ ይሆነዋል ተብሎ ሲታሰብ የተወሰነበትን የእስር ዘመን በሙሉ ሳያጠናቅቅ ሊፈታበት የሚችልበት አሠራር ነው። የአመክሮ ጥያቄ የዕድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው 20 ዓመት ከታሰረ በኋላ ነው ሊያቀርበው የሚችለው ነው። ጥያቄውን ራሱ ተቀጪው ወይም የሚመለከተው አካል ሊያቀርበው ይችላል። ጥያቄው የቀረበለት ፍርድ ቤትም በወ/ሕ/አ 202 መሰረት በእስር ላይ እያለ የተረጋገጠ የጠባይ መሻሻል ማሳየቱን፣ ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን ካሳ መክፈሉን ሲያረጋግጥ አመሉና ፀባዩ በአመክሮ ቢፈታ መልካም ውጤት ያስገኛል ብሎ ሲያምን እስረኛው በአመክሮ እንዲፈታ ይወስናል። ጥፋተኞች ሲታሰሩ የአመክሮ ዕድል ተጠቃሚ የሚያገኙት ምን ሁኔታዎችን ሲያሟሉ እንደሆነ የሚታሰሩበት ተቋም የማሳወቅ ግዴታ በወ/ሕ/አ 203 ላይ ተጥሎበታል።
በአመክሮ መፈታት የፈተና ጊዜ ነው። ቀሪውን የእስራት ዘመኑን ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ጊዜ የእድሜ ልክ እስር ሲሆን ደግሞ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ እስረኛው ከእስር ተለቆ ይፈተናል። የተወሰነለትን የጠባይ ደንብ ከጣሰ ወይም አዲስ ወንጀል ከፈፀመ በተሰጠው የሙከራ ዕድል መጠቀም ባለመቻሉ በወ/ሕ/አ 206 መሰረት አመክሮው ተሽሮ ቀሪ ቅጣቱን ይፈፅማል። አዲስ ወንጀል የፈፀመ በአመክሮ ላይ ያለ ሰው የደጋጋሚነት ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በአመክሮ የተቀነሰለት ቅጣት እና የአዲሱ ወንጀል ቅጣት ተደርቦ ይፈፀምበታል።
ሠ. መሠየም
መሠየም ማለት የተወሰነበትን ቅጣት የፈፀመ ቅጣቱ በይርጋ በይቅርታ የቀረለት፣ በአመክሮ ወይም በገደብ የታገደለት ማንኛውም ሰው በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ከቅጣቱ በፊት የነበረው ስም እንዲመለስና ፍርዱ አንዲሰረዝለት በወ/ሕ/አ 232 መሰረት የሚጠይቅበት ሥርዓት ነው። ሕጉ መሠየም የሚገኘው በመልካም ሥራ እንጂ እንደ መብት ይገባኛል የሚባል አለመሆኑን ደንግጓል። ተቀጪው ከሞተ ወይም ችሎታ ካጣ የቅርብ ዘመዶቹ ወይም ወኪሉ ጥያቄውን ሊያቀርቡ ይችላሉ።
መሰየም የሚፈቀደው ቅጣቱ ካለቀበት ወይም ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ አምስት ዓመት ወይም በሌላ ቀላል ሁኔታዎች የሁለት ዓመት ጊዜ ካለፈ በኋላ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ግለሰቡ ፀባዩ መልካም ከሆነና ወንጀል ካልፈፀመ እንዲሁም አቅሙ እና ሁኔታው በሚፈቅድለት መልኩ በፍርድ የተወሰነበትን ወይም ሊከፈል ይገባዋል ተብሎ የሚገመትበትን ካሳ፣ የዳኝነት እና ማናቸውንም ኪሳራ ከከፈለ ቅጣቱ በይርጋ የታገደለት ሰው ደግሞ ቅጣቱ ቢፈፀም ከሚጠናቀቅበት ጊዜ በፊት ልዩ ወይም የሚያስመሰግን ወታደራዊ ወይም ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ካላበረከተ በቀር መሰየም ሊፈቀድለት አይችልም።
መሠየም በቅጣት የቀረ የመብት፣ የማዕረግ ወይም ችሎታ ማጣት ቀሪ ሆኖ ሕዝባዊ እና ቤተሰብ የማስተዳደር የሙያ ሥራ የመሥራት መብቱን እንደገና እንዲያገኝ እንደሚያደርገው በወ/ሕ/አ 235 ላይ ተደንግጓል። በተጨማሪም ፍርዱ ከወንጀለኞች መዝገብ ላይ ተሰርዞ ወደፊትም እንዳልተፈረደበት የሚቆጠር ሲሆን በጠላትነት ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ያለፈውን ጥፋት አንስቶ መውቀስ ወቃሹን በስም ማጥፋት በወንጀል ያስቀጣል። ለሕዝብ ጥቅም የተደረገ ነው ብሎ መከራከሪያ ማቅረብም አይቻልም። ጥያቄው የሚቀርበው ፍርድ ቤት ሲሆን፣ ፍርደ ቤቱ ጥያቄውን ካልተቀበለው ከሁለት ዓመት በፊት ድጋሚ የመሠየም ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም። በወ/ሕ/አ 237 መሠረት መሰየም ከተፈቀደ በአምስት ዓመት ጊዜ እንደገና በሞት ወይም በፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል የሠራ እና የተፈረደበት ሰው መሰየሙ ይሰርዝበታል። ዳግመኛም የመሠየም ጥያቄ ማቅረብ አይችልም።