የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል፡-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

10 Mons Ago 608
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል፡-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
 
ኢንስቲትዩቱ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ እየተጠናከረ እንደሚሔድ ገልጿል።
 
የሚጠበቀው እርጥበት የመካከለኛ ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት፣ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት እንደሚረዳ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ነው ያስታወቀው።
 
በዚሁ ወቅት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ስፍራዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅም ነው የገለፀው።
 
በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ አመላክቷል፡፡
 
በዚሁ የክረምት ወቅት የሚኖረው እርጥበት የሰብሎችን የውሃ ፍላጎት ለማሟላት፣ የግብርና ተግባራትን ለማከናወን፣ ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለግጦሽ ሳር ልምላሜም አዎንታዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታውቋል።
 
እንዲሁም በተፋሰሶች ያለውን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሃብትን ከማሻሻል እና የግድቦችንና የወንዞችን የውሃ መጠን ከማሳደግ አንጻር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሷል፡፡
 
በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚኖረው ከባድ ዝናብ በማሳዎች ላይ የውሃ መተኛት፣ የአረም መስፋፋት ሊከሰት እንደሚችልም አመልክቷል።
 
በተጨማሪም ከእርጥበት ጋር የተያያዙ የሰብል በሽታዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ቅድመ ዝግጀት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
 
የሚኖረው ዝናብ ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ነው ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል ፡፡
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top