ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የአረፋን በዓል አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በማሰብ እንዲያከብር ሸይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ አሳሰቡ

7 Mons Ago 545
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የአረፋን በዓል አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በማሰብ እንዲያከብር ሸይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ አሳሰቡ
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የ1445 ዓ.ሒ. የዒድ አል-አድኃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር ካለው ላይ ለአቅመ-ደካማ ወገኖቹ እንዲያካፍል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ አሳሰቡ።
 
ሸይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ ይህን ያሳሰቡት የዒድ አል-አድኃ በዓልን ምክንያት በማድረግ አስቀድሞ በተቀረፀ መልዕክታቸው ነው።
 
የአረፋ ቀን አሏህ (ሱ.ወ.) ፀጋውን የለገሳቸው ሙስሊሞች የዑዱሂያ እርድ የሚያከናውኑበት መሆኑን የጠቀሱት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ እነዚህ ሙስሊሞች ከሚያርዱት እርድ ለተቸገሩ ወገኖቻቸው፣ በተለይም ለአቅመ ደካማና በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ማካፈል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
 
"እጅግ በጣም አዛኝና ሩኅሩኅ የኾነው ጌታችን አሏህ (ሱ.ወ.) ይቅር ባይነትን ይወዳል" ያሉት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ "ተበድሎ ይቅር ያለን ሰው አሏህ (ሱ.ወ.) የሠራውን ጥፋት ይቅር የሚለው በመኾኑ፣ ሁላችንም ይቅር ልንባባል ይገባል" ብለዋል።
 
የዘንድሮውን ዒድ አል-አድኃ (አረፋ) ለየት የሚያደርገው የሀገራችን የኢትዮጵያ ልጆች ሀገራዊ ምክክር እያደረጉ የሚገኙበት ወቅት ላይ በመሆኑ ነው ብለው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለጋራ ሀገራችን ሰላማዊነት ጠቃሚ መኾኑን በመረዳት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በያለበት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
 
ሀገራዊ ምክክሩ ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት ጠቅላይ ምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያዎችን፣ ዓሊሞችን፣ ምሑራንን፣ ታዋቂ ግለሰቦችንና ለሀገር የሚያስቡ ሰዎችን በማሰባሰብ፣ የሙስሊሙን ጥያቄዎች በማደራጀት ለሚመለከተው አካል መላኩን ሸይኽ ሐጂ ተናግረዋል።
 
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን የተናገሩት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም፤ ሁሉም የሰላም ዘብ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈው፣ ለሀገራችንና ለመላው ዓለም ሙስሊሞች በዓሉ የደስታ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top