ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ የግንዛቤ ማነስ፣ የአቻ እና የቤተሰብ ግፊት ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ገፊ ምክንያቶች ናቸው-የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

1 Mon Ago
ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ የግንዛቤ ማነስ፣ የአቻ እና የቤተሰብ ግፊት ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ገፊ ምክንያቶች ናቸው-የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎች ከሀገራቸው ወጥተው ለመሄድ የሚጠቀሙበት መደበኛ ያልሆነ መንገድ ነው፡፡
 
በዚህ ሂደት ውስጥ በድንበር ጠባቂዎች ከሚሰነዘር ጥቃት ጀመሮ የአካል ብሎም ህይወት እስከማጣት የሚደርስ አደጋ አንደሚያጋጥም በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍ እና ክትትል ስራ አስፈፃሚ ደረጀ ተግይበሉ ለኢቢሲ ሳይበር ተናግረዋል።
 
የዝውውር ሂደቱ በተለይ ለሴቶች እና ህፃናት ከባድ እንደሆነም ነው ሥራ አስፈጻሚው የገለጹት::
 
ችግሮችን አልፈው ካሰቡበት ሀገር ሲደርሱም ሌላ እክል ይገጥማቸዋል የሚሉት ሥራ አስፈፃሚው በአሰሪዎች የሚደርስ አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ ብሎም ተገቢ ጥቅምን ማጣት እንደሚጠቀሱ አንስተዋል፡፡
 
አቶ ደረጀ አያይዘውም ከሚደርስባቸው የወንጀል ጥቃት ባሻገር እነርሱም የወንጀል ድርጊት እንዲፈፅሙ ይገደዳሉ ያሉ ሲሆን ይህም ከውንብድና እስከ ህገወጥ ታጣቂ ቡድን አባልነት የከፋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
የዝውውር ሂደቱን ለመግታት የፍትህ አካላት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ አዘዋዋሪዎችን የመያዝ እና የመጠየቅ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
 
አሁን ላይ በድንበር አካባቢዎች ላይ በመቀናጀት እና ወንጀለኞቹን በመለዋወጥ ቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
 
ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ማህበረሰብ የማንቃት ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል::
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top