የቱ ነው ቀዳሚው ሰላም? ወይስ ፍትሕ?

10 Days Ago
የቱ ነው ቀዳሚው ሰላም? ወይስ ፍትሕ?

ሰላም የአንድ ማህበረሰብ ዋስትናው ነው፡፡ ወጥቶ ለመግባት፣ ሰርቶ ለመለወጥ እንዲሁም ያሰቡትን ለማሳካት የሀገር ሰላም ወሳኝ ነው፡፡

ፍትሕ ከፍርድ ባሻገር በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ብሎም በፖለቲካው ያለ እኩልነት እንደሆነ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡

በዚህም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ሂደት ውስጥ የጠፉ ጥፋቶች የፍትሕ አሰጣጥ እንዴት ይታያል ሲል ኢቢሲ ሳይበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ሰላም እና ፍትሕ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡

የሰላም መስፈን ፍትሕን ፤የፍትሕ መከበር ሰላምን ያመጣሉ የሚሉት ባለሙያው ሰላም የፍትሕ  መሰረቱ መሆኑንም ነው የሚያነሱት፡፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መርሆዎች ሰላም ማስፈን፣ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ እና መልሶ ማቋቋም የሚሉ ሲሆኑ እነዚህን ለመተግበር ሰላም አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

ሰላም በማስፈን ሂደት የመንግሥት ሃይል እንደሚያስፈልግ ያነሱት ባለሙያው፤ በውይይት የሚፈቱትን በውይይት ከዚያ ውጪ የሚሆኑትን መንግሥት የተደራጀ አቅሙን በመጠቀም ሰላምን ሊያሰፍን ይገባል ይላሉ፡፡

የሚገኘውን ሰላም ለማዝለቅ መንግሥት የሽግግር ፍትሕ መርህ ሥርዓትን መተግበር እንዳለበትም ነው የገለፁት፡፡

መንግሥት የአካባቢ ሰላምን በማስፈን ላይ አተኩሮ ከሰራ በኋላ ለተበደሉ አካላት ፍትሕ እና ካሳ ማሰጠት የሚሉት ሃሳቦች  በተከታይነት የሚመጡ መሆኑን በመግለጽ፤ የመንግሥት ቁርጠኝነት የሚታይባቸው ነጥቦች እንደሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ለዘመናት የተፈፀሙ እና አሁንም የቀጠሉ ያልጠሩ ትርክቶች፣ ቁርሾዎች፣ አለመተማመኖች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ የሰላም እጦቶች እና እነዚህን አስታከው የሚፈፀሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይስተዋላሉ።

ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና ሁሉን አቀፍ ፍትሕ ለማስፈን ሀገሪቱ በተሟላ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንድታልፍ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ስለመሆኑ በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን የተደረገ ጥናት አረጋግጧል።

በዚህም የሀገሪቱን ነባራዊ  ሁኔታ ያገናዘበ የሕግ የበላይነት እና ፍትሕን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሽግግር ፍትሕ ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ወጥቷል።

ይህ ፖሊሲ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና የሕግ የበላይነትን ወይም ፍትሕን ከማስፈን አንጻር እንዴት ይታያል? 

በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ሰብዓዊ  መብት ድርጊት መርሃሐ-ግብር ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት  አወል ሱልጣን  ሰላም ለሁሉም ነገር ምሰሶ መሆኑን አንስተው፤ ከምንም በፊት ቀድሞ መረጋገጥ ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የአማራጭ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለህዝቡ በማጋራት ከ80 በላይ የሚሆኑ የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰው፤ ከእነኚህ ውስጥ 49 የሚሆኑት በሁሉም ክልሎች የተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ውይይት ከተደረጉባቸው አካባቢዎች መካከል የፀጥታ ችግር ያለባቸው ከተሞችም እንደተካተቱ ነው የጠቀሱት፡፡ 

በዚህም ትግበራው ላይ ተመሳሳይ ቆራጥነት ሊታይ እንደሚገባም አንስተዋል።

በቀጣይ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ከመተግበር አንጻር በፖሊሲው ላይ የተመላከቱ አቅጣጫዎችን ወደ መሬት የማውረድ ስራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ቅድመ ሁኔታን ከግምት ያስገባ የምህረት አሰጣጥ፣ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማድረግ፣ እርቅ እንዲሁም የማካካሻ ሥርዓት እና ተቋማዊ ግንባታ የሽግግር ፖሊሲው መተግበሪያ ስልቶች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ሰላምን በማስከበር  ሂደት ውስጥ የመንግስት ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፤ መረጋጋት በሌለባቸው ቦታዎች “የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ምን አይነት እርምጃዎችን መውሰድ አለበት?” የሚለው ጉዳይ በቀጣይ በፍኖተ ካርታው እና ፍኖተ ካርታውን ተከትሎ በሚዘጋጁ ሰነዶች አማካኝነት በሚቀመጥ አቅጣጫ መሰረት በጥንቃቄ ሊመራ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ይህም በቀጣይ በሚቋቋም አደረጃጀት መሰረት የሚመራው የፖሊሲ ትግበራ ምዕራፍ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ባስገባ መልኩ በጥናት ላይ በተደገፈ ሁኔታ  እንደሚመሩ  ነው የተናገሩት፡፡

ከምንም በፊት ሰላም ይቀድማል ያሉት ኃላፊው፤ ይሁንና ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሳይተገብር መቆየቱ ደግሞ ችግሩን ከማባባስ ያለፈ ሚና አይኖረውም ብለዋል፡፡

የትግበራ ምዕራፉ ለግጭት መንስዔ ለሆኑት ጉዳዮች እልባት ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ሰላምን ለማስፈን የራሱን ሚና ይጫወታል ይላሉ፡፡

በአፎሚያ ክበበው

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top