ከወለጋ እስከ ጎጃም የተገኘው ሰላም

7 Mons Ago 851
ከወለጋ እስከ ጎጃም የተገኘው ሰላም

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሰላም መደፍረሶች ተስተውለዋል፡፡
በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ በወለጋ ዞኖች እና በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሰላም ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡

በዚህም የአካባቢው ማህበረሰብ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጦ የቆየ ሲሆን ማህበረሰቡ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል፤ ለሞት እና እንግልትም ተዳርጓል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ግን የመከላከያ ሠራዊት በእነዚህ አካባቢዎች ባደረጋቸው የሰላም ማስከበር ሥራዎች ዛሬ ላይ በአካባቢዎቹ የሰላም አየር እየነፈሰ ነው፡፡

የኢትጵያ ቴሌቪዥን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከነበሩት ከተሞች አንዷ በሆነችው ጊምቢ ከተማ ተገኝቶ ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡

ነዋሪዎቹ ባለፉት ጊዜያት በከተማዋ እጅግ አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፋቸውን ገልጸው፣ አሁን የተገኘው ሰላም መንግሥት ህግን ለማስከበር እና ሰላምን ለማስፈን ባደረገው ጥረት የመጣ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን የሚያስታውሱት ነዋሪዎቹ ከዚህ ቀደም በነበረው ጊዜ በርካታ ህጻናት እና አዋቂዎች ለሞት መዳረጋችውን፣ ብዙዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ላይ የተገኘው ሰላም ህዝቡን ያሳረፈ መሆኑን እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ያደረጉት የሰላም ጥሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ እፎይታ የሰጠ መሆኑን ገፀዋል፡፡

ነዋሪዎቹ አክለውም ህዝቡም ከመንግሥት ጋር በመሆን ጠላት ያጠፋውን ለመመለስ እና ወደ ልማት ለመግባት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

ሌላኛዋ ሰላም እርቋት የሰነበተችው የደብረማርቆስ ከተማ በአሁኑ ሰዓት ሰላም መስፈኑን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ወደ ከተማዋ ባቀናበት ወቅት ለመታዘብ ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋ ከዚህ ቀደም በጦርነት መክረሟን ያስታውሳሉ፤ ይሄንንም ተከትሎ ማንኛውንም ነዋሪ ወጥቶ መግባት እንኳን ያልቻለበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበርም ይናገራሉ፡፡

ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ሳቢያም ብዙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡

ካለፉት ሁለት እና ሶስት ወራት ወዲህ ግን በከተማዋ ሰላም መገኘቱን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፣ አሁን ላይ እንደልብ ወጥተው መግባት መቻላቸውን፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ መጀመራቸውን እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡

በከተማዋ የተገኘው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የታጠቁ አካላት በማስተዋል ወደ ምክክር እና እርቅ እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡


የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ የሆኑት መንበሩ ዘውዴ በበኩላቸው ከተማዋ ባለፉት ጊዜያት ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባት ይገልጻሉ፡፡

አሁን ላይ በተገኘው ሰላም የመንግስት ተቋማት ወደ ሥራ መመለሳቸውን የወደሙ ስፍራዎችን መልሶ የማልማት ሥራን ከህብረተስቡ ጋር በመሆን መጀመሩን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

የከተማዋ ጸጥታ ወደነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ የመከላከያ ሠራዊት ከማህበሰቡ ጋር በመሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉንም ይናገራሉ፡፡

ከምንም በላይ ሰላም አስፈላጊ ነው የሚሉት ከንቲባው፣ የአማራ ክልል ህዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በጦርነት አለመሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግ እና ወደ ሰላም መምጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ያለው የጦርነት ችግር ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጣ እየተሠራ ያለ ሥራ መኖሩን ገልጸው፣ ጦርነትን አማራጭ አድርገው የሚመለከቱ አካላት ቆም ብለው እንዲያስቡ እና ወደ ሰላም መንገድ በመምጣት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ከንቲባው ጠይቀዋል፡፡

የዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ምሁር የሆኑት አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ወደ ፊት እንድትራመድ ካስፈለገ በውስጥ ሰላሟ መመስረት አለበት ያሉ ሲሆን፣ ህዝቦቿ ከዘለቂ ንትርክ መውጣት እንዳለባቸው ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ኋላቀር የሆነ የትግል ዘዴ ይዘው የሚታገሉ ወገኖች ወደ ሰላም መድረክ ሊመጡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከሰላማዊ መንገድ ይልቅ በመሳሪያ ጥያቄያቸውን ለማስመለስ የሚሞክሩ አካላት ልብ ገዝተው በዓለም ታሪክ በጦርነት የተገኘ ድል አለመኖሩን በመረዳት እና ከጎረቤት ሀገሮች ትምህርት በመውሰድ ፊታቸውን ወደ ሰላም ያዙሩ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ማህብረሰቡ የጦርነት አስከፊነትን ተረድቶ ቁጭ ብሎ በመነጋገር በሀገሩ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲመሰረት መርዳት አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢትጵያን ሰላም የመጠበቅ ህገ መንግሥቱን እና ሥርዓቱን መጠበቅ የሁሉም ድርሻ ነው ያሉት ባለሙያው፣ እዚህ ላይ በትኩረት መሠራት አለበት ሲሉ በአፅንኖት ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ደያሞ ዳሌ ደግሞ ምሁራን በሀገራዊ ጉዳዩች ላይ በባለቤትነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ልዩነቶችን በምክክር መፍታት ይገባል የሚሉት ባለሙያው በተከፈተው የሰላም በር በመግባት የሰላም በሮችን ማስፋት ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል

ሀገሪቷ ሲንከባለሉ ለመጡ ችግሮቿ መፍትሔ ለማምጣት ያቋቋመቸው ሀገራዊ ምከክር ኮሚሽን እና የሽግግር ፍትህ ሰላምን ለማምጣት እየሄዱበት ያለው መንገድ ተስፋ የሚሰጥ ነው፤ የሚሉት ባለሙያው ሁሉም በኃላፊነት ስሜት በመሳተፍ ሰላምን እውን ማድረግ አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተስሊም ሙሀመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top