መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ መረጋጋት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው፡- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

11 Days Ago
መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ መረጋጋት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው፡- የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ በተወሰነ መልኩ የታየውን የዋጋ ቅናሽ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
 
በተወሰነ መልኩ የታየውን የዋጋ መረጋጋት ለማስቀጠል ምርታማነት ላይ አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድ እና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ መስከረም ባሕሩ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልጸዋል።
 
ከዚህ ቀደም በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የተስተዋለው የዋጋ ግሽበት እንዲረጋጋ በቂ ምርት ማምረት ላይ ትኩረት መደረጉን መሪ ስራ አስፈፃሚዋ አስታውሰው፤ ምርቱ ለሸማቹ በአግባቡ እንዲዳረስ ማድረግ መቻሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገም ነው ያነሱት።
 
ምርት ለሸማቹ በአግባቡ እንዲደርስ የገበያ መሰረተ ልማቶች መሟላታቸው አሰራሩን እንዳቀለለው ነው የተናገሩት።
 
ምርት ከማሳ ተነስቶ ሸማቹ ጋር በሚደርስበት ሂደት ውስጥ በመካከል በመግባት ለዋጋ መጨመር ምክንያት የሚሆኑ አካላትን ለማስወጣት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት መሪ ስራ አስፈፃሚዋ፤ በቂ ምርት መመረት መቻሉ የእነዚህን አካላት ተሳታፊነት ይቀንሰዋል ብለዋል።
 
በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ወጥነት ማጣት ብዙ ምክንያቶች እንዳሉት የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ ተቋሙ የተለያዩ የሀገሪቷን ክፍሎችን በመቃኘት ለምርት እና ምርታማነት ብሎም ተደራሽነት ተግዳሮት እየሆኑ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top