የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ከታክስ በፊት 3 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

10 Mons Ago 692
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ከታክስ በፊት 3 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በግማሽ ዓመቱ ከታክስ በፊት 3 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።
 
ተቋሙ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከሚሰጠው አገልግሎቶች እና ከሌሎች የገቢ ምንጮች17 ነጥብ 23 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 23 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንም ጠቁሟል።
 
በሺፒንግ ዘርፍ፣ በጭነት አስተላላፊነት፣ በወደብና ተርሚናል አገልግሎት እንዲሁም በኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን የተገኘ ገቢ ስለመሆኑም ነው የተገለጸው።
 
በግማሽ ዓመቱ የድርጅቱን መርከቦችና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም 1 ሚሊዮን 886 ሺህ 399 ቶን ዕቃ ለማጓጓዝ ታቅዶ፤ 2 ሚሊዮን 214 ሺ 156 ቶን ማጓጓዝ መቻሉም ተጠቅሷል።
 
የገቢ እና ወጪ ኮንቴይነር ፍሰት 197 ሺ 699 ኮንቴይነር ለማጓግዝ ታቅዶ 204 ሺ 358 ኮንቴነር ማስተናገድ መቻሉን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
 
ድርጀቱ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ከመደገፍ እና አትራፊነቱን ጠብቆ ከመቀጠል በተጨማሪ ወጪ ንግድን ለማበረታት መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፤ በማኑፋክቸሪንግ እና በወጪ ንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ እና ለተፈቀደላቸው ባለሃብቶች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።
 
ድርጅቱ ከሚሰጣቸው ድጋፎች ውስጥ በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ለምርት ግብዓትነት ለሚያስገቧቸው ጥሬ ዕቃዎች ፣ከየብስ ትራንስፖርት የትርፍ ህዳግ እንዲሁም ከባሕር ትራንስፖርት የትርፍ ህዳግ የዋጋ ቅናሽ ማድረግ ይገኙበታል ተብሏል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top