የሸገር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ለታማኝ እና ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች ዕውቅ እና ሽልማት ሰጥቷል።
በዕውቅና እና ሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ ቱሉ፤ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛን ጨምሮ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲቄዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
180 የሚደርሱ ግብር ከፋዮች ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 5 የሚሆኑ ግብር ከፋዮች ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል።
በከተማዋ 49 ሺህ የሚደርሱ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ በዚህ ወቅት ተናግረዋል።
ከንቲባው በተያዘው በጀት ዓመት ግብር ከሚከፍለው ማህበረሰብ 27 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ጠቅሰው፤ በበጀት ዓመቱ 6 ወራት 14.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
በሸገር ከተማ በ2016 ዓ.ም የተሰበሰበው ግብር 16.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር ተገልጿል፤ በዚህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በበጀት ዓመቱ 6 ወራት የተሻለ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ነው የተነገረው።
አሁን የተሰበሰበው ገቢ በቂ አለመሆኑን የገለጹት ከንቲባው፤ ከተማዋ ዘመናዊ ሆስፒታል እና ዮኒቨርሲቲ የሌላት በመሆኑ በቀጣይ የተሻለ ግብር በመሰብሰብ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ይሰራል ብለዋል።