አርጀንቲና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር በማሳደግ በትምህርቱ ዘርፍ በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ኢግናሲዮ ሮካታግሊታ ገለጹ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ኢግናሲዮ ሮካታግሊታ ጋር በትምህርት ዘርፉ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ሁለቱ ሀገራት በሚኖራቸው የጋራ ትብብር በትምህርቱ ዘርፍ ሊሰሩባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮችን አብራርተዋል።
በተለይም በቋንቋ ልማት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችና መምህራን ልውውጥና ነጻ የትምህርት እድል፣ በኪነ ጥበብ፣ ስፖርትና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር መስራት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩንም ጨምረው ጠቅሰዋል።
አምባሳደር ኢግናሲዮ ሮካታግሊታ በበኩላቸው፤አርጀንቲና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር በማሳደግ በትምህርቱ ዘርፍ በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን የትምህር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አክለውም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችና መምህራን ልውውጥና ነጻ የትምህርት እድል፣ በአዳዲስ ፈጠራዎች፣ በኪነ ጥበብ፣ ስፖርት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡