የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት በከተማዋ የቱሪስት ፍሰት ላይ አመርቂ ውጤት አምጥቷል፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

2 Days Ago 150
የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት በከተማዋ የቱሪስት ፍሰት ላይ አመርቂ ውጤት አምጥቷል፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማትና አጠቃላይ የመልሶ ማልማት ስራ በከተማዋ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አመርቂ ውጤት ማምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
 
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሥድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
 
በሪፖርቱም 4 ሚሊዮን 424 ሺህ 62 የሀገር ውስጥና 546 ሺህ 443 የውጪ ሀገር ቱሪስቶች በሥድስት ወራቱ ከተማዋን መጎብኘታቸውን ከንቲባዋ ጠቅሰዋል።
 
በዚህም 96.8 ቢሊዮን ብር ወደ ከተማዋ የግልና የመንግስት ገቢ (ኢኮኖሚ) ፈሰስ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት።
 
2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ከመጀመሪያው የኮሪደር ልማት በፍጥነት እና በጥራት እየተተገበረ እንደሆነም ገልጸዋል።
 
የኮሪደር ልማት ሥራው 3ሺ 515 ሄክታር ቦታን የሚሸፍን ሲሆን 246 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ፣ 431 ሄክታር የአረንጓዴ ቦታዎች ግንባታ፣ 141 ኪ.ሜ የብስክሌት መንገድ፣ 53 የህፃናት መጫወቻዎች፣25 የታክሲና አውቶቢስ መጫኛና ማውረጃ፣ 8ዐ የመኪና ማቆሚያዎች እና 23 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ያካትል ብለዋል።
 
በመልሶ ማልማቱ ለተነሱ ነዋሪዎች ወደ 9 ሺህ የሚደርሱ የመኖሪያ ቤቶች፣1ሺህ 402 የመስሪያ ሼዶች፣ 200 የንግድ ሱቆች፣ 2ሺህ 124 የመስሪያ ቦታዎች የተላለፉ ሲሆን ወደ 3 ሺህ ለሚደርሱት ደግሞ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ቋሚ የሥራ እድል እንዲያገኙ መደረጉን ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አብራርተዋል።
 
ለተገኘው ውጤት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ አባባ እንደ ስሟ ውብ፣ አበባና፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ እንድትሆን ሌት ተቀን እየሰጡት ላለው አመራር፣ ክትትልና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top