በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር የህዝብን ተጠቃሚ ለማሳደግ እንደሚሰራ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ ገለጹ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ዋና አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት 6 ወራት በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል።
በግብርናው ዘርፍ የውሃ አማራጮች እና ግብዓቶችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መሰራቱን በአወንታ ጠቅሰዋል።
በማህበራዊ ዘርፍ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን አስታውሰዋል።
በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረም የተጀመሩ ጥረቶች ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በቀጣይም በክልሉ የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አፈ ጉባዔዋ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የምክር ቤት አባላት ለሕዝብ አንድነትና ትስስር በሚበጁ ስራዎች ላይ በተማኮር ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አሳስበዋል።