በምገባ መርሐ ግብር ስራ 20 ሺህ ገቢ ያልነበራቸው እናቶች ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

3 Days Ago 109
በምገባ መርሐ ግብር ስራ 20 ሺህ ገቢ ያልነበራቸው እናቶች ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተማሪዎች እና በማህበረሰብ ምገባ መርሐ ግብር ስራ 20 ሺህ የሚሆኑ ገቢ ያልነበራቸው እናቶች ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የከተማዋ አስተዳዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
 
ምክር ቤቱ በጉባዔው የከተማ አስተዳደሩን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሥድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በመወያየት የቀሪ ወራት ዋና ዋና አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
 
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ባለፉት 6 ወራት የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ጥቅል የሥራ እቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
 
በሪፖርቱ በምገባ መርሐ ግብር ስራ 20 ሺህ የሚሆኑ ገቢ ያልነበራቸው እናቶች ቋሚ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተጠቅሷል።
 
አዲስ አበባ በአፍሪካ ሕጻናት ዕድገት ምቹ እንድትሆን ለማስቻል በቀዳማይ የልጅነት ፕሮግራም በ3 ዓመት ለ1000 ህፃናት ማቆያ ለማቋቋም በዕቅድ መያዙ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
 
በዚህም የግሉን ዘርፍ ጨምሮ 822 ማቆያ የተቋቋመ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉም ተጠቁሟል።
 
ባለፉት ስድስት ወራት ከ 11 ሺህ 900 ነፍሰ-ጡር ሴቶች፣ አጥቢ እናቶችና ሕፃናት የቀጥታ አልሚ ምግብ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉንም ገልፀዋል።
 
ለሰንበት ዝግ በሚደረጉ መንገዶች በርካታ ሕጻናት የመጫወቻ ስፍራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉም በሪፖርቱ ተነስቷል።
 
በነገዋ የሴቶች ተሃድሶና የልቀት ማዕከል ለከፍተኛ ማህበራዊ ችግር የተጋለጡ 302 ሴቶች በመጀመሪያ ዙር ሰልጥነው ለእያንዳንዳቸው ስራ በመፍጠር ስምሪት መሰጠቱንም ገልፀዋል።
 
ለ7 ሺህ 591 አረጋውያን እና ለ1 ሺህ 605 አካል ጉዳተኞችም መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎት፣ የስነልቦና፣ የማህበራዊ እና የተሃድሶ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል።
 
ለ582 አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉም ተጠቅሷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top