88ኛው የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ በአዲስ አበባ ሥድስት ኪሎ የሰማዕታት ሐውልት እየተከበረ ይገኛል።
የዛሬ 88 ዓመት በዚህ ዕለት ፋሽስት ጣሊያን ከየካቲት 12/1929 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት ከ30 ሺህ በላይ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በነበሩ ንፁሃን ዜጎችን ጭካኔ በተሞላበት አኳኋን በጅምላ ጨፍጭፏል።
ይህንን የኢትዮጵያን ነፃነት በማስጠበቅ ሂደት የተከፈለ መስዋዕትነት በማሰብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አባት አርበኞች በየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ስር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
የአበባ ጉንጉኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች የአርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ ለመጭዉ ትዉልድ በሚያስቡ ጀግኖች መስዋዕትነት ነፃነቷን ከእነ ክብሯ ጠብቃ የቆየች መሆኗን በመገንዘብ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ማስቀጠል የዚህ ትዉልድ ኃላፊነት መሆኑ በመታሰቢያ በዓሉ ላይ ተገልጿል።
በበዓሉ ላይ የሐይማኖት አባቶች፣ የአርበኞች ልጆችና ሌሎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።