መሻታችን ግቡን እንዲመታ ከወጣቶች ጋር የተሳሰረ አሰራር መገንባት ያስፈልጋል፦ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ

14 Days Ago 152
መሻታችን ግቡን እንዲመታ ከወጣቶች ጋር የተሳሰረ አሰራር መገንባት ያስፈልጋል፦ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ
መሻታችን ግቡን እንዲመታ ከወጣቶች ጋር የተሳሰረ አሰራር መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ተናገሩ።
 
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው 21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ ነው።
 
የጸረ-ሙስና ትግልን ውጤታማ አድርጎ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ለምናደርገው ጥረት እና ለዚህ መሻታችን ሥነ ምግባር እና ስርዓትን አስማማተው የያዙ ወጣቶች ሊኖሩን ይገባል ብለዋል።
 
ሙስናን ለመከላከል እና ለማጥፋት ብዙ ሥራዎች ቢሰሩም ከታሰብው ግብ አልደረሰም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣በወጣቶች ላይ መስራት እንደሚገባ አጽናኦት ሰጥተዋል።
 
ለዚህ ደግሞ የመጪው ጊዜ ቃል ኪዳን በተባበሩት መንገስታት ድርጀት ተዘጋጅቶ የጸደቀ ስምምነት መኖሩን አስታውሰው፤ የዚህ ስምምነት ዋና ግብ በፀረ-ሙስና ትግል ወጣቶችን ማሳተፍ መሆኑንም ተናግረዋል።
 
ለዚህም ተቋማዊ አሰራርን ማጽናት፣ የተቋማትን መናበበ እውን በማድረግ እና በትምህርት ተቋማት የሞራል እና ግብረ ገብ ትምህርት በመስጠት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
 
ሙስና ለረጅም ጊዜ ያቆየናቸውን ማህበራዊ ወረቶችን ሁሉ የሚያሽመደመድ፣ እድገትን የሚሰብር እና የነገውን ትውልድ ጥሪት የሚያሟጥጥ በሽታ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
 
ይህንን በሽታ ሃሳባዊም ባሕላዊም ሽፋን እየሰጠነው እንዳንጠየፈው አድርገነው ቆይተናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች በሽታውን እንደካባ ለብሰው ለመንቀሳቀስ አያፍሩም ብለዋል።
 
እንዲህ ያለውን በሽታ ለማጥፋት የወጣቱን ሥነ ምግባር በሚገነቡ የሚዲያ ሥራዎች በማገዝ የተቀናጀ ሥራ መስራት እንደሚገባም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።
 
በመርሃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ፣በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ የምክር ቤት አባላት፣ የፌደራል የስነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
 
ዛሬ የማጠቃለያ መድረኩ እየተካሄደ ያለው 21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን "ወጣቶችን ያማከለ የፀረ-ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top