"በመካከላችሁ ምክክር ይኑር" የሚለው የቁርዓን አንቀፅ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን ሀገርን ጭምር የሚመለከት ነው፦ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ

2 Mons Ago
"በመካከላችሁ ምክክር ይኑር" የሚለው የቁርዓን አንቀፅ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን ሀገርን ጭምር የሚመለከት ነው፦ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ

"ሀገራዊ ምክክር" የሚለውን ሀሳብ "በጎ ነገር ሁሉ መልካም ነው" በሚለው ብሂል መሰረት መቀበል ተገቢ ከመሆኑ በተጨማሪ፤ "ምክክር" የሚለው ቃል ቁርዓናዊ መሰረት ያለው መሆኑን ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ ገለጹ።

የእስልምና ሐይማኖት መምህሩ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ሀገራዊ ምክክር ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን በመጥቀስ፤ "አላህ በመካከላችሁ  ምክክር ይኑር” ሲል የደነገገው ትዕዛዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

“በመካከላችሁ ምክክር ይኑር” የሚለው የቁርዓን አንቀፅ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን ሀገርን ጭምር የሚመለከት ነው ብለዋል።

“የእስልምና እምነት ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ በጣም ትልቅ ነው፤ ከጌታችን አላህ ምርጥ ስሞች መካከል አንዱ ‘አሰላም’ (ሰላም) የሚለው ነው” ሲሉ አመላክተዋል።

"በየዕለቱ 5 ጊዜ ሰላት ሰግደን (ጸሎት አድርገን) ስናበቃ የምንደመድመው ‘አላህ ሆይ፥ አንተ ሰላም ነህ፤ ሰላም የሚመነጨው ከአንተ ነው’ በማለት ነው፤ ይህ ደግሞ እስልምና ለሰላም ያለውን ትልቅ ቦታ ያሳያል" ነው ያሉት።

ሀገራዊ ምክክሩ አንዱ ተሸናፊ፣ አንዱ አሸናፊ በማይሆንበት መንገድ የሚካሄድ በመሆኑ፤ እንደ እስልምና አስተምህሮ የተበደለ ሰው ይቅርታ ቢያደርግ ትልቅ ይባላል እንጂ አያንስም ብለዋል።

እንዲህ ያለው ምክክር ለሀገር እና ለትውልድ የሚበጅ፣ አሉ የተባሉ ችግሮችንም ለመፍታት የሚጠቅም ነው፤ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በቀናነት በሚደረግ ምክክር እንጂ፣ “እኔ ያልኩት ካልሆነ” በሚል ግትር አቋም አይደለም ብለዋል። 

"በእስልምና አስተምህሮ ጌታችን አላህ (ሱወ) ታላቁን ነቢይ ሙሐመድን (ሰዓወ) የላካቸው በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እና ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር እንዲፈቱ ነው፤ እኛም ይህን ተምሳሌት መተግበር ሐይማኖታዊም ሀገራዊም ኃላፊነታችን ነው" ብለዋል።

"ሀገራዊ ችግር ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊ ችግር እንኳ የሚፈታው በምክክር ነው" የሚሉት ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ፤ ከዚህ ውጪ ሀገሪቱን የምናድንበት መንገድ የለም ሲሉ አመላክተዋል።

ለሀገራዊ ችግር መፍትሔ የመሻትን ኃላፊነት ለአንድ ወገን መተው ተገቢ አለመሆኑን ያነሱት የሐይማኖት መምህሩ፤ የመፍትሔው አካል መሆን ከሁሉም ኢትዮጵያውያን  ይጠበቃል ብለዋል።

ለልጆቻችን፥ ከሐብት ይልቅ ሰላማዊ ሀገርን ማውረስ ይገባናል፤ ሐብት ያለ ሰላም ጠፊ ነውና ሲሉም አሳስበዋል።

በሜሮን ንብረት

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top