በትግራይ ክልል የትራኮማ በሽታን ለመከላከል የመከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
ክትባቱ እየተሰጠ ያለው ጤና ሚኒስቴርና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ "ላይት ፎር ዘ ወርልድ" ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ቡድን መሪ አቶ አረጋይ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በሁለተኛው ዙር ለሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች የትራኮማና የፀረ-ተህዋሲያን ክትባት እየተሰጠ ነው።
የትራኮማ በሽታ በዋነኝነት በንፅህና ጉድለት እንደሚከሰት ጠቁመው፣ በተለይ ህፃናት ለበሽታው የተጋለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በበሽታው መንስኤና መከላከያ መንገዶች ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ ለበሽታው መዛመት እንደአንድ ምክንያት ሊቆጠር እንደሚችልም አስረድተዋል።
የትራኮማ በሽታን በወቅቱ ካልታከሙት ለዕድሜ ልክ አይነ-ስውርነት የሚዳርግ በመሆኑ ክትባቱን በአግባቡ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት።
ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የክትባት መርሃ ግብር እያከናወነ መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በክልሉ በመጀመሪያው ዙር ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች ተመሳሳይ ክትባት መሰጠቱን ቡድን መሪው አስታውሰዋል።
እንደ ሀገር የትራኮማ በሽታ የህብረተሰቡ የጤና ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።