የባሕር በር መኖር አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም፡- አምባሳደር ቶፊቅ አቡዱላሂ አህመድ

10 Mons Ago 626
የባሕር በር መኖር አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም፡- አምባሳደር ቶፊቅ አቡዱላሂ አህመድ
የባሕር በር አስፈላጊነት ለአንድ ሀገር እድገት ካለው ጠቀሜታ አንጻር አጠያያቂ አይደለም ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ቶፊቅ አቡዱላሂ አህመድ ገለጹ።
 
አምባሳደር ቶፊቅ አቡዱላሂ አህመድ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ "የዲፕሎማሲያችን መጠናከር ማሳያ የሚሆኑ እልፍ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም፤ በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረምነው ስምምነት አንዱ ነው" ብለዋል።
 
የባሕር በር አስፈላጊነት ለአንድ ሀገር እድገት ያለው ጠቀሜታ አጠያያቂ አይደለም የሚሉት አምባሳደር ቶፊቅ፤ በዓለም ላይ አብዛኛው የንግድ ልውውጥ በመርከብ በሚከናወንበት በዚህ ወቅት፤ የባሕር በር ያለው እና የሌለው ሀገር የሚኖረው ተጠቃሚነት እኩል እንዳልሆነ ይገልጿሉ።
 
ለባሕር በር እና ተጓዳኝ ለሆኑ ጉዳዮች የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፤ አሁን ላይ አካባቢውን ለማልማት ማዋል መቻሉ ትልቅ ዕድል መሆኑን ያስረዳሉ።
 
በስምምነቱ የሚገኘው ኮሪደር፤ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በሌሎች ሀገራት አሰራር እና ሕግ ሳይሆን በኢትዮጵያ አሰራር እና ጥበቃ ስር ይሆናል ነው ያሉት። በዚህም የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ አስተማማኝ የሆነ የባሕር መውጫ እና መግቢያ ማግኘት እንደሚያስችል ያብራራሉ።
 
አሁን ላይ የምንተባበርባቸው መስኮች እየሰፉ እና እየበዙ ነው የሚሉት አምባሳደር ቶፊቅ፤ የባሕር በር ጉዳይ ወሳኝ እና አንገብጋቢ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል ሲሉም ያመላክታሉ።
 
ለሀገር እድገት በሚጠቅሙ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ላይ የሀገር ውስጥ አንድነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ፤" እርምጃችንን ለማምከን እና ለማጠልሽ የሚደረጉ ጥረቶችን በማስወገድ ለብሔራዊ ጥቅማችን በጋራ ልንቆም ይገባል" ብለዋል።
 
ከሀገራት ጋር የሚኖረንን ዲፕሎማሲ በማጎልበት እና የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በመመስረት፤ ሌሎች መልከ ብዙ ጥቅሞችን ለሀገራችን ማስገኘት አለብን ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top