ለኩላሊት መድከም እና ለልብ ሕመም የሚዳርገው የቶንሲል በሽታ

1 Yr Ago
ለኩላሊት መድከም እና ለልብ ሕመም የሚዳርገው የቶንሲል በሽታ
በጉሮሯችን ውስጥ የሚገኙት የቶንሲል ዕጢዎች በጀርሞች ተጠቅተው ሲቆጡ እና ሲያብጡ የሚከሰተው ሕመም ቶንሲላይተስ (የቶንሲል ሕመም) እንደሚባል የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የቶንሲል ሕመም (ቶንሲላይተስ) በብዙ ሰዎች ዘንድ በየጊዜው የሚያጋጥም የሕመም ዓይነት ሲሆን አንድ ሰው በየዓመቱ በአማካይ እስከ አራት ጊዜ ያህል በቶንሲል ሕመም ሊጠቃ ወይም ቶንሲላይትስ ሊይዘው ይችላል።
ብዙውን ጊዜ የቶንሲል በሽታ በልጆች ላይ የሚከሰት ሲሆን በባክቴሪያ የሚከሰተው የቶንሲል በሽታ ከ 5 እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ላይ ባሉ ልጆች ላይ በጣም የተለመደ ነው።
👉 የቶንሲል ሕመም መንሥኤዎች
አብዝሃኛው የኅብረተሰብ ክፍል የቶንሲል ሕመም ቀዝቀዛ ምግብን ወይም መጠጥን አብዝቶ መጠቀም ወይም በኃይለኛ የፀሐይ ሙቀት በመመታት ይከሰታል ብሎ ያምናል።
ነገር ግን በሽታው በባክቴሪያ እና በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር እንደሆነ እና ተገቢውን ሕክምና በወቅቱ ካላገኘ እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
እንደ አይስክሬም ያሉ ቀዝቃዛ ምግቦችን በተለይ ለሕፃናት መስጠት፣ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች በፀሐይ ላይ መመገብ እና በከባድ ፀሐይ መመታት ከቶንሲል ሕመም ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸውም ይናገራሉ።
በቫይረስ የሚከሰተው የቶንሲል ሕመም በአብዛኛው በቀላል የቤት ውስጥ ሕክምናዎች እንደሚድን የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በባክቴሪያዎች በተለይም ስትሬፕቶኮክስ ፓዮጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ የሚመጣው የቶንሲል ሕመም ዓይነት ግን ለከፍተኛ ሕመም እና ስቃይ የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል መዘዝ የሚያስከትል መሆኑን ያስገነዝባሉ።
በባክቴሪያ ሳቢያ በሚመጣው የቶንሲል ሕመም የተያዘ ሰው በአግባቡ እና በወቅቱ ሕክምናውን ካላገኘ ከኩላሊት መድከም (ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆም) እስከ ልብ ሕመም፣ የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) የቆዳና የጉሮሮ ኢንፌክሽኖች ብሎም እስከ ሞት ሊያደርሱ የሚችሉ መዘዞችን ያስከትላል።
👉 የቶንሲል ሕመም ምልክቶች
ኃይለኛ ትኩሳት፣ ከባድ የራስ ምታት፣ መጥፎ ጠረን ያለው ትንፋሽ፣ የጉሮሮ ሕመም፣ ለመዋጥ መቸገር፣ በጉንፋን የተዘጋ ጉሮሮ፣ የሆድ ቁርጠት፣ ቀይ ያበጠ ቶንሲል፣ አገጭ ስር የሚገኙ ሊምፍ ኖዶች ላይ የሚፈጠር ማበጥ እና በአንገት ግራ እና ቀኝ አካባቢ በእጅ ሲነካ የሕመም ስሜት መኖር ዋንኞቹ የበሽታው ምልክቶች ናቸው።
ባክቴሪያ ወለዱ የቶንሲል ሕመም ከመደበኛው የቶንሲል ሕመሞች ምልክቶች በተጨማሪ ከሚኖረው የበሽታው ምልክት መካከል በጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ በሚኖረው እብጠት ላይ ነጫጭ አይብ መሰል ነጠብጣቦች /ሽፍታዎች/ ሊታዩበት ይችላሉ።
የሚሰማቸውን የሕመም ስሜት መግለጽ በማይችሉ ጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚታዩ የቶንሲል ሕመም ምልክቶች፦ ምግብ ሲበሉ በሚሰማቸው ሕመም ምክንያት ልሃጫቸውን ማዝረክረክ፣ ምግብ ለመብላት ፍላጎት አለማሳየት እና ያለወትሮ የመፍዘዝ ስሜት መታየት መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
👉 የቶንሲል ሕመም መተላለፊያ መንገድ፦
የቶንሲል ሕመም በትንፋሽ አማካይኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ እና ሕፃናትን በይበልጥ የሚያጠቃ የበሽታ ዓይነት ነው።
👉 የቶንሲል ሕመም ሕክምና
የቶንሲል ሕመም ሕክምና ሕመሙን እንዳስከተለው ተህዋስያን ዓይነት እንደሚለያይ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በቫይረስ ምክንያት የሚመጣን የጉሮሮ ሕመም ሰውነታችን ባለው የበሽታ መከላከል አቅም የሚዋጋ ሲሆን መድኃኒት መውሰድ አስፈላጊ አይሆንም።
በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰትን የጉሮሮ ሕመም ሕክምና ቦታ በመሄድ ባክቴሪያ አጥፊ መድኃኒቶችን (Antibiotics) መውሰድ ተገቢ ነው።
ነገር ግን ሕመሙ በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ የተከሰተ መሆኑን ለመለየት ሕመሙ በተከሰተ ቅፅበት ወደ ሐኪም ቤት ሄዶ ማረጋገጥ እንደሚገባ ባለሙዎቹ ይመክራሉ።
ቶንሲልን በቀዶ ጥገና ማስወገድ የቶንሲል ሕመምን ለማከም አዝውትሮ የሚውል ሕክምና የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን በሽታው የሚደጋገምባቸው ሰዎች ላይ ብቻ የሚውል የሕክምና ዘዴ ነው።
በአንድ ዓመት ውስጥ 7 ጊዜ ያህል የሚደጋገምባቸው ሰዎች ወይም ለ3 ዓመት በየዓመቱ ሦስት ጊዜ ለሚታመሙ ሰዎች የሚታዘዝ መፍትሔ ነው።
በቶንሲል ሕመም ምክንያት የሚከሰቱ ሌሎች የጤና ችግሮች ካጋጠሙ የቶንሲል ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልግ እንደሚችልም ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የቶንሲል ሕመም ያለበት ሰው በቶሎ ከሕመሙ ለመዳን በቂ ዕረፍት መውሰድ፣ ሻይ፣ ወተት፣ ሾርባ እና አጥሚት የመሳሰሉ ትኩስ ፈሳሽ መውሰድ፣ ለስለስ ያሉ ምግቦችን መመገብ፣ ለብ ባለ ውኃ በጨው እና ዝንጅብል መጉመጥመጥ፣ አንድ ብርጭቆ ውኃ ውስጥ አራት ማንኪያ ማር፣ ሩብ ማንኪያ ጨው እና የሎሚ ጭማቂ ጨምሮ በማዋሃድ በቀን ከ2 እስከ 3 ጊዜ መጠጣት ጥሩ ወጤት እንደሚያስገኝ የሕክምና ጠበብቶች ይመክራሉ።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top