ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

1 Yr Ago
ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

 ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

********************

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ 2.52 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ መደበኛ ጉባኤው የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል። 

የአፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ፣ በተጠቀሰው ወራት ከዘርፉ 2.77 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ገልጸው የዕቅዱ 91 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ከወጪ ንግድ ግብርናው ከፍተኛው ድርሻ ይዟል 

ከግብርናው 1.75 ቢሊዮን፣ ከኢንዱስትሪ ዘርፉ 320.9 ሚሊዮን ዶላር፣ ከማዕድን ዘርፍ 389 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች ተጨምረውበት በድምሩ 2.52 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ስምንት ወራት የተገኘው ገቢ አምና በተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 2.10 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።

ባለፉት ስምንት ወራት በሀገሪቱ ኑሮ ውድነት እንዲከሰት ያደረጉት ውስጣዊ እና ውጫዊ ተፅኖዎች እንዳሉ አቶ ገብረመስቀል ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፋም መንግሥት የውጭ ምንዛሪ መድቦ ለአምራች ኢንዱስትሪው ድፍድፍ የምግብ ዘይት እንዲቀርብ በማድረግ 103 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በሀገር ውስጥ ተመርቶ ተሰራጭቷል።

10.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ተፈፅሞ ወደ ሀገር እየገባ ሲሆን ተጨማሪ የምግብ ዘይት እንዲገባ ግዢ ተፈፅሞ እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል።

የስንዴ ፍላጎት ጉድለትን ለማሟላት ከተፈፀመው የ4 ሚሊዮን ኩንታል ግዢ ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ለማሰራጨት ታቅዶ 670 ሺ ኩንታል ተሰራጭቷል።

ኢትዮጵያ የወጪ ገቢ ንግድን ለማሳደግ በዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢቶች ላይ መሳተፏን ገልፀዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ጥያቄዎች 

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለውን የኑሮ ውድነት መንግሥት ለምን በዝም ተመለከተ? የነዳጅ አጥረት፤ የሲሚኒቶ፣ የብረት እና የቆርቆሮ ዋጋ ለምን ጭማሪ አሳየ? ሲሉ የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ከአባላቱ ጥያቄ አቅርበዋል።

ለኑሮ ውድነቱ ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩክሬን እና ሩስያ መካከል የተከፈተው ጦርነት በሀገር ውስጥ ደግሞ ስግብግብ ነጋዴዎች በሚፈፅሙት መሰረታዊ ሸቀጦችን የመደበቅ እና ዋጋ የመጨመር ድርጊቶች መሆናቸውን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ገልጸዋል።

መንግሥት ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ በማውጣት ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በወይንሸት ደጀኔ

 

ግብረመልስ
Top