35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ተጽዕኖዎች እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

2 Yrs Ago
35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ተጽዕኖዎች እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ተጽዕኖዎች እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

 

35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ብዙ ተጽዕኖዎች እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የዘንድሮው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ፣ በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ፣የአሜሪካ አዲሱ ቋሚ መልዕክተኛ ወደ አዲስ አበባ መምጣት እና ባለፉት ቀናት የተሰሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች ቃል አቀባዩ መግለጫ የሰጡባቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡

35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከጥር 25 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት ፕሬዘዳንቶች ፣ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ጋዜጠኞች፣የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እና የበለጸጉ አገራት ተወካዮች እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

ይህ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ተጽዕኖ ተደርጎ እንደነበር የተናገሩት አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም ፣ጦርነት ላይ ናት፣ ኮሮና ቫይረስም እየተስፋፋ ነው የሚሉ ሀሳቦች ዋነኞቹ ምክንያቶች ነበሩም ብለዋል።

ይሁንና ውሳኔውን ለሚወስኑ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በተሰራ ስራ ውሳኔውን መቀልበሱን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ መሪዎች ጭምር ባደረጉት ጥረት ጉባኤው በአዲስ አበባ መሪዎች በአካል እንዲያካሂዱ መወሰኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። ትኩረቱን በአፍሪካ አልሚ ምግብ ዙሪያ እንደሚያደርግ በተገለጸው የዘንድሮው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

አምባሳደር ዲና የመሪዎቹ ጉባኤ በአዲስ አበባ በአካል እንዳይካሄድ ተጽዕኖ ያደረጉ አገራት እነማን ናቸው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ጉባኤው በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ ግፊት ሲያደርጉ የነበሩ ሀገራትን ማንነት መገመት ይቻላል ይሁንና የአገራቱን ስም ዝርዝር አንናገርም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ አገር እንዲዛወር ግፊት አለ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም አምባሳደር ዲና ግፊቶች በተለይም ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ የገባች ሲመስላቸው የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ እንዲነሳ ግፊት ማድረግ የተለመደ ነውም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከመሪዎች ጋር ተወያይተዋል፤ ይህ ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ጋር ያለንን ግንኙነት አይጎዳም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ኢትዮጵያ አሁንም ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና አልሰጠችም ሲሉ መልሰዋል፡፡

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top