በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ

2 Yrs Ago
በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ

በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ አስታውቀዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያውን ውይይት ተጨማሪ በጀቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ተገልጿል።

ተጨማሪውን በጀት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ በቀጥታ ወደ ስራ እንደሚገባም ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

መንግስት ከሚመድበው መነሻ በጀት በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተለይም ከዓለም ባንክ ለመልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠበቅ አቶ አህመድ ገልጸዋል።

የመልሶ ማቋቋም መርሀ ግብሩ በመንግስት የሚመራ፣ የተቀናጀ፣ በየደረጃው በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ ተጠያቂነት ያለውና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚተጋ መሆኑንም አስረድተዋል።

በውይይቱ የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የስራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መስሪያ ቤት አመራሮች መገኘታቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top