በጋምቤላ ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች ፈቃድ ተሰጥቷል፦ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

6 Hrs Ago 85
በጋምቤላ ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች ፈቃድ ተሰጥቷል፦ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

በጋምቤላ ክልል ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 161 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱም የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በክልሉ ያለው ሰፊ ለም መሬት ለዘመናዊ እርሻ አመቺ በመሆኑ አልሚ ባለሀብቶች በግብርና እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሰማርተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡

በክልሉ በአቦቦ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አልሚዎች ሰሊጥና ማሾን ጨምሮ በገበያ ላይ ተፈላጊና የውጭ ምንዛሪን በሚያስገኙ ምርቶች ላይ በማተኮር እያለሙ መሆናቸውን ለኢቲቪ ተናግረዋል።

በተያዘው አመት ከ300 ለሚበልጡ አዳዲስ አልሚዎች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ እስካሁን ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 161 አልሚ ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ (ዶ/ር) ተናግረዋል። 

ፈቃድ ከተሰጣቸው አልሚዎች መካከል 99 ያህሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት። 

ፕሮጀክቶቹ ወደ ስራ ሲገቡ ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩም አስረድተዋል፡፡

በሚፍታህ አብዱልቃድር


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top