በመሪዎች ጉብኝት ይበልጥ የጠነከረው  የኢትዮ-ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

8 Hrs Ago 171
በመሪዎች ጉብኝት ይበልጥ የጠነከረው  የኢትዮ-ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

በርካታ ምዕተ ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በንግድና በመሰረተ ልማት ግንባታም የታጀበ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

በተለይ በመጀመሪያ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ ፈረንሳይ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል እንዳልነበር እስከዛሬም የሚታወስ ጉዳይ ነው። 

የሀገራቱ ግንኙነቱ ሲጠናከር  ፈረንሳይ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የወዳጅነት ቢሮዋን ከመክፈት አልፋ እ.አ.አ. በ1907 በመዲናዋ ኤምባሲዋን  በመክፈት የዲፕሎማሲ ግንኙነቱ ስር እንዲይዝ አድርጋለች።  

የኢትዮ-ፈረንሳይን የዘመናት ግንኙነት በተለያዩ ጊዜዎች ከፍ ዝቅ እያለ ቢቀጥልም በመሪዎች ደረጃ ጭምር ትብብሮችን ለማጠናከር ያለሙ ጉብኝቶች ተደርገዋል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በ2011 እና በ2015 ዓ.ም በፈረንሳይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን የሰሞኑ ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜያቸው ነው።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው በ2011 እና በ2017 ዓ.ም በይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደኢትዮጵያ መምጣታቸው አይዘነጋም።

ከሰሞኑ ከቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር ልዑካቸውን ይዘው ወደፓሪስ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ኤሊሴ ቤተመንግሥት በወታደራዊ ትርዒት የታጀበ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው የሀገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ውይይት በሀገራቱ መካከል የተደረሱ ስምምነቶችን አፈፃፀም መገምገማቸውን መሪዎቹ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ግንኙነታችንን እና ትብብራችንን በሚያጠናክሩ ሰፋ ያለ መጠነ ርዕይ ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መወያየት ምንግዜም አስደሳች ነው" ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት ትብብር በብዙ ጠቃሚ ዘርፎች የቀጠለ መሆኑን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ትስስር የበለጠ ማሳደግ ከቅድሚያ የትኩረት ማዕከሎቻቸው አንዱ መሆኑን ነው የገለጹት።

"ለተደረገልን ደማቅ አቀባበል እና በታኅሳስ ወር በአዲስ አበባ ከነበረን ውይይት ቀጥለን ስላካሄድነው ፍሬያማ ውይይት ምስጋናዬን እገልፃለሁ" ሲሉ አስፍረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የፈረንሳይ ጉብኝትም በቅርስ ጥበቃና ዕድሳት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በወታደራዊ ድጋፎች ላይ የጎለበተውን የሁለቱን ሀገራት ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛል።

ሁለቱ ሀገራት በሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች፣  በባህል እና  ቱሪዝም ዘርፎች ለረጅም ዘመናት የቆየ ጠንካራ ትስስር የፈጠሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በፓሪስ የተደረገው የመሪዎቹ ውይይት በኢኮኖሚው መስክ የበለጠ ትብብር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ከፓሪስ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዘገባው የተጠናከረው የአፍሪካን ኢንተለጀንስ እንዲሁም የተለያዩ የፈረንሳይ የዜና አውታሮችን ዋቢ በማድረግ ነው።

በጌትነት ተስፋማርያም


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top