ፕሮፌሰር ኤልሣቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ጥናት አስደናቂ ምሁር እና ከፍተኛ ተሟጋች ነበሩ። ስለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ በማስተማር እና በማጥናት የማይደበዝዝ አሻራቸውን ትተው አልፈዋል።
በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኪነ-ጥበብ የጋራ መገለጫ እንዲሆን እና የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ አስደናቂ ሥራ ሠርተዋል።
ፕሮፌሰር ኤልሣቤጥ ወልደጊዮርጊስ፣ ከእናታቸው ወ/ሮ ዋካ ድንቄ እና ከአባታቸው ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ግንቦት 1 ቀን 1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ።
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በናዝሬት ት/ቤት ተምረዋል።
የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአሜሪካ ከሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚከስ ትምህርት ተከታትለው በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። በዚህ ሙያቸውም እዚያው አሜሪካ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ አገልግለዋል።
በተለይ ለሥነ-ጥበብ እና ለታሪክ በነበራቸው ልዩ ዝንባሌ እንዲሁም እስክንድር ቦጎስያንን ከመሳሰሉ ሠዓሊዎች እና የጥበቡ ማኅበረሰብ ጋር በነበራቸው የጠበቀ ወዳጅነት ወደ ጥበብ ዓለም በመሳባቸው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በሙዝየም ጥናት ዶክትሬታቸውን ደግሞ በሥነ ጥበብ ታሪክ እና ሂስ ከኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በ2000 ዓ.ም አግኝተዋል።
ለዶከትሬት ትምህርታቸው የመመረቂያ ጽሑፍ ዘመናዊነት እና የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ላይ በማተኮር ያካሄዱት ጥናት እና ምርምር በ2011 ዓ.ም "Modernist Art in Ethiopia" በሚል ስያሜ ለታተመው መጽሐፋቸው ዋነኛው እርሾ ነበር።
ይህ በኦሀዮ እና በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ ፕሬስ ለሕትመት የበቃው መጽሐፍ በርካታ አንባቢ ያተረፈ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እና ሽልማት የተቸረው ሰነድ መሆን ችሏል።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋምን የመምራት ኃላፊነት ተረክበው ከ1996 እስከ 2002 ዓ.ም በዳይሬከተርነት አገልግለዋል።
በዚህ የኃላፊነት ዘመናቸው የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም እንደ ዳርፉር ባሉ ወሳኝ በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች እና በሌሎችም ሀገር አቀፋዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውይይቶች ዙሪያ ጉባኤዎችን በማሰናዳት ብቻ ሳይሆን፣ ተቋሙ ከዚያ ቀደም በነበረው የረዥም ዘመን ልምድ እና እውቀት ላይ በመገንባት የበለጠ እንዲደራጅ እና ከብሩን እና የዕውቀት ሃብቱን እንዲያሳድግ ጉልህ ደርሻ አበርክተዋል።
በመቀጠልም በዩኒቨርሲቲው የቴአትር ጥበባት፣ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እና የአለ ሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት ተቀናጅተው “እስክንድር ቦጎስያን የክወና እና የዕይታ ጥበባት ኮሌጅ" እንዲቋቋም በማስቻል ኮሌጁ ከተመሠረተበት ከ2001 እስከ 2004 ዓ.ም በዲንነት አገልግለዋል።
በተጨማሪም በአለ የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት የፊልም እና የሥነ-ጥበብ ድኅረ-ምረቃ ትምህርት ከፍልን በማቋቋም ሂደት የበኩላቸውን ሚና የተጫውተዋል።
በዚሁ ትምህርት ክፍል በማስተማር፣ የተማሪዎቻቸውን የሥነ-ጥበብ እሳቤ፣ ዕውቀት እና ልምምድ እንዲዳብር የነበራቸው አስተዋጽዖ ከልዩ ሙያዊ አበርከቶዎቻቸው እንዱ ሲሆን፣ ይህንኑ ተግባራቸውን አሁን በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ የቀድሞ ተማሪዎቻቸው በኩራት የሚመሰከሩት ዕውነት ነው።
ለሀገራችን ብቸኛ የሆነው የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ቤተ-መዘክር ገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል መሥራቾች አንዷ ናቸው። ቤተ-መዘክሩ ከተቋቋመበት ከመስከረም 2001 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዙሮች ሁለት ጊዜ በዳይሬከተርነት መርተውታል።
ፕሮፌሰር ኤልሣቤጥ ስለ ዘመናዊነት በኢትዮጵያ፣ ስለ ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ፣ ስለ ከተሜነት እና በተለያዩ ማኅበረሰብ ተኮር ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ሲምፖዝየሞች፣ ኮንፍረንሶች እና ውይይቶችን አዘጋጅተዋል።
በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ውስጥ የቪዡዋል አርት፣ የባህል እና የሥነ-ጽሑፍ ውጤቶች ያላቸውን ግንኙነት የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶችን አካሂደዋል።
በሥዕል ጥበብ ላይ የሚታዩ አዳዲስ ግኝቶች ከዘመናዊነት ፍልስፍና እና ርዕዮተ-ዓለማዊ ትረካዎች ጋር እንዴት እንደተሳሰሩ በዝርዝር ዳስሰዋል። በጥናታቸውም ኪነ-ጥበብ ለኢትዮጵያ ምሁራዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ታሪክ ታላቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን አመላክተዋል።
በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያሳተሙ ሲሆን፣ የትራንዚሽን መጽሔት አዘጋጅ እና ቦርድ ሰብሳቢ፣ የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ጥናት ጆርናል (NEAS) እንዲሁም የኢትዮጵያ ጆርናል ኦፍ ሶሻል ሳይንስ ኤንድ ሂውማኒቲስ (EJOSSAH) አባል ነበሩ።
በተጨማሪም ጆርናል ፎር ክሪቲካል አፍሪካን ስተዲስ (JCAS)፣ ካላሉ አርትስ እና የደቡብ እስያ፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ (CSAAME) ንጽጽር ጥናት አዘጋጅ አማካሪ እና የቦርድ አባልም ነበሩ።
በአፍሪካ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ዓለም አቀፍ ጥናቶች የአሊ ማዝሩይ አንጋፋ ፕሮፌሰር ሆነው ሠርተዋል። በብራውን ዩኒቨርሲቲ እና በቪየና በሚገኘው መልካም ሥነ-ጥበብ ተጋባዥ ፕሮፌሰር እንዲሁም በጣሊያን ሮክፌለር ቤላጊዮ ማዕከል ተባባሪ ባልደረባ ነበሩ።
የአፍሪካ ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም እና ሥርዓተ ትምህርቱ እንዲዳብር ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ሲሆን፣ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙ ዕውቅና እንዲያገኝ ታላቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
"Modernist Art in Ethiopia" የተሰኘው መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ ዘመናዊ ኪነ-ጥበብ ላይ ሰፊ ምሁራዊ ትንታኔያቸውን የያዘ ነው።
መጽሐፉ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ኪነ-ጥበብ ላይ የተጻፈ የመጀመሪያው ትልቅ መጽሐፍ እንደሆነ ከአፍሪካ ኢንቲትየት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
መጽሐፉ በአፍሪካ ጥናት ማኅበር የዩናይትድ ኪኒግደም ‘ፌጅ’ እና ኦሊቨር ለሽልማት ታጭቷል። የአፍሪካ ጥናት ማኅበር ምርጥ መጽሐፍ ተሸላሚ ነው። የአፍሪካ ጥናት ማኅበር የ2020 "Bethwell A. Ogbot Book Prize for the best book on East African Studies" ተሸላሚም ነው።
ፕሮፌሰር ኤልሣቤጥ በአፍሪካ፣ በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ እና በመላው አፍሪካ የዘመናዊ የሥነ ጥበብ ታሪክ ፋኩልቲ (MAHASSA) አባል ሆነው አገልግለዋል። በበርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች እና ሴሚናሮች ላይ ኢትዮጵያን እና አፍሪካን ወክለው ተሳትፈዋል።
በሥነ ጥበብ ታሪክ፣ በሙዚየሞች ጥናት እና በአፍሪካ ጥናት መስኮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደሩ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን እና በግላቸው 14 ጥናቶችን ማሳተማቸውን በአፍሪካ ኢንሰቲትዩት ገጽ ላይ የቀረበው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያን ኪነ-ጥበብ ዘመናዊነት ለመቃኘት እና ለማጉላት የሠሩት ሥራ በዳበረው የአፍሪካ ሥነ-ጥበብ እና ታሪክ ላይ ትልቅ ግንዛቤ እንዲፈጠር አስችሏቸዋል።
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ ውስጥ በምትገኘው እና በዓለም ደረጃ የባህል እምባ እየተሰኘች በመጣቸው የሻሮዣ ከተማ በዓለም አቀፍ ጥናት ዩኒቨርስቲ (Global Studies University) የአፍሪካ ኢንስቲትዩት የአሊ መዝሩዊ ቀዳሚ ከፍተኛ ፌሎ በመሆን ተቀላቅለዋል።
በተቋሙ የድኅረ ምረቃ እና የዶክትሬት ትምህርት ክፍል ምሥረታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን፣ በተጓዳኝ የሂውማኒቲስን ትምህርት ከፍል በመምራት፤ ካሪኩለም በመቅረፅና በማስተማር አዲስ ለተከፈቱት የትምህርት መርሐ ግብሮች አገልግሎት ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር ኤልሣቤጥ ወልደጊዮርጊስ ለሥራ በሄዱበት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በ69 ዓመታቸው ድንገት ሕይወታቸው አልፏል።
ባገለገሉበት የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ራስ መኮንን አዳራሽ የመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ከተካሄደ በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቀብራቸው ተፈጽሟል።
እርሳቸው በአካል ቢለዩንም ሥራዎቻቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምሁራንን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን እና ተመራማሪዎችን ማነቃቃቱን ይቀጥላል።
የአካዳሚክ ማኅበረሰቡም እርሳቸውን በማጣቱ እጅግ ቢያዝንም የአፍሪካን ሥነ-ጥበብ እና ባህል ለማስተዋወቅ የሠሩትን ሥራ በማስቀጠል ዓላማቸውን ከግብ እንደሚያደርስ ይታመናል።
በለሚ ታደሰ