ኢ-መደበኛ የጎዳና ላይ ንግድን ሕጋዊ ሥርዓት ለማስያዝ የወጣው ደንብ በመደበኛ ነጋዴዎች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመከላከል እንደሚረዳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ እንደገለፁት፤ ከዚህ ቀደም የጎዳና ላይ ንግድን ለመቆጣጠር የወጣው 88/2009 ደንብ አሁን ካለው ንግድ ሥርዓት ጋር የማይሄድ በመሆኑ አዲሱ ደንብ እንዲወጣ ተደርጓል።
ኢ-መደበኛው ነጋዴ ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዲያስገኝ እና ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር ያለውን ትስስር ለማስቀረት ደንቡ ማስፈለጉን ነው የገለጹት።
ኢ-መደበኛ የጎዳና ንግድ ማለት የንግድ ፈቃድ ሳያወጣ በጎዳና ላይ እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ አነስተኛ ካፒታል ባላቸው ሰዎች የሚደረግ ንግድ እንደሆነ ቢሮው አስታወቋል።
እነዚህ ነጋዴዎች በደንቡ መሰረት በሚደራጅ የአሰራር ሥርዓት መሰረት ፈቃድ እንደሚያወጡ እና በተፈቀደላቸው ጎዳና ላይ በደረት ላይ በሚያንጠለጥሉት ፈቃድ መሰረት የሚሠሩ እንሚሆን ተጠቅሷል።
ነጋዴዎቹ የሚመዘገቡበት ቋት በዚህ ደንብ መሰረት እንደሚደራጅ ያስታወቀው ቢሮው፤ ከተመዘገቡበት አካባቢ ውጭ ሲገኙ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተጠቅሷል።
እነዚህ ነጋዴዎች በሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ የትራፊክ ፍሰት በማይበዛባቸው መንገዶች ላይ ፈቃድ በማውጣት እንደሚሠሩ እና ይህንንም የሚያስፈጽም አካል በደንቡ መሰረት እንደሚደራጅ ታውቋል።
የኢ-መደበኛ ነጋዴዎቹ በሁለት ዓመታት ውስጥ ካፒታላቸው 200 ሺህ ብር የሚደርስ ከሆነ ወደ መደበኛነት እንሚገቡም የንግድ ቢሮው አስታውቋል።
የሚይዟቸው ዕቃዎች የጥራት መስፈርትን ያሟሉ መሆን እንዳለባቸው እና የሚበላሹ እና ለጤና ጠንቅ የሚሆኑ ዕቃዎች ደግሞ ክልከላ እንደሚደረግባቸው ነው የተነገረው።
ይህንን የንግድ ሂደት ሥርዓት ለማስያዝ እና ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥም በከተማዋ ከንቲባ የበላይ ጠባቂነት የሚመራ ግብረ-ኃይል እንደሚቋቋም ተልጿል።
ይህ ደንብ የከተማውን ፀጥታ፣ የትራፊክ እንቅስቃሴ እና ውበቷን ለመጠበቅም እንደሚረዳ ተመላክቷል።