የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ክልል የላካቸው 85 የእርሻ ትራክተሮች በክልሉ ለሚገኙ ዞኖች ዛሬ ርክክብ ተደርጓል።
በርክክቡ ወቅት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ ኢያሱ አብረሃ(ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በዘመናዊ የግብርና አሰራር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ኃላፊው በእርሻ ትራክተሮቹ በኩታ ገጠም የተደራጁ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመው፤ለተደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።
የእርሻ ሜካናይዜሽን ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀው፤ በክልሉ የአርሶ አደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
አክለውም ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ከአጋር አካላት የተገኙ 125 ትራክተሮች ተከፋፍለው ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።
በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽንን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ ምርታማነትን በጥራትና በመጠን በማሳደግ አግሮ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።