ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችን አመሰገኑ

5 Days Ago 1280
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችን አመሰገኑ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ባለፉት ሁለት ዓመታት ጦርነት እንዳይከሰት ለተጫወቱት ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፣ “ባለፉት ሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ በምክትል ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ እና ጻድቃን ገብረ ተንሣይ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተጨማሪ ጦርነት እንዳይፈጠር እና ያሉ ጥያቄዎች በንግግር እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል” ብለዋል።

“ምንም እንኳን ቀድሞ በነበረው ውጊያ ብንወቅሳቸውም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰጡት አመራር ግን ማድነቅ እና ማመስገን እንፈልጋለን፤ ተጨማሪ ውጊያ እንዳይነሣ ሙከራ አድርገዋል” ሲሉም አክለዋል።

ለአመራሮቹ የተሰጠው የሁለት ዓመት ጊዜ አሁን ስላለቀ ተጨማሪ ማሻሻያ የሚፈልግ ጉዳይ እንዳለም ጠቁመዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አፈፃፀም ተገምግሞ መጠነኛ ለውጥ ተደርጎ የፕሪቶሪያን ስምምነት በሚያከብር መንገድ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ሥራውን እየሠራ ሕዝቡን ለምርጫ ማዘጋጀት እና ሕዝቡን የሥልጣን ባለቤት የማድረግ ሒደት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ይህንን ለማድረግ ከፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ እና ምክትል ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ እንዲሁም ጻድቃን ገብረ ተንሣይ ጋር ልዩ ልዩ ውይይቶችን ሲያደርጉ እንደነበር አንሥተዋል።

የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦችም መቅረባቸውን ጠቁመው፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል ካሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ንግግር እየተደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በንግግሩ መሠረት ሕግ ተሻሽሎ መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ሊካሄድ እንደሚችል ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የነበረው ሥራ ተገምግሞ በጠንካራ ጎናቸው ተወድሰው፣ በደካማ ጎናቸው ተወቅሰው የሚቀያየሩ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል።

ዮናስ በድሉ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top